የኢትዮጵያ ሴቶችና 'ማርች 8'

306

ሰለሞን ተሰራ (ኢዜአ) 

ጊዜው ከ100 ዓመት በፊት ነው እለቱ ደግሞ እአአ መጋቢት 8 ቀን 1908፤ በኒውዮርክ ከተማ በሺዎች የሚቆጠሩ ፋብሪካ ውስጥ የሚሰሩ ሴቶች እየደረሰባቸው ያለውን ኢፍትሃዊነትና በሴቶችና በወንዶች መካከል እኩልነት አለመስፈኑን ለመቃወም አደባባይ ተገኙ፡፡ በወቅቱ ብዙዎቹ ሴቶች ረዥም ሰአት ቆመው ማሽን ላይ ይሰራሉ፣ የልብስ ስፌት መኪኖች ላይም ረዥም ሰአት ያሳልፋሉ፡፡ አጠቃላይ ስራ ላይ የሚያሳልፉት ሰአት በቀን ከ12 እስከ 14 ሰአታት ነበር፡፡ ለዚህ አድካሚ ስራ የሚከፈላቸው ክፍያ አነስተኛ ከመሆኑ ባሻገር በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሰርተው አልፈው የጡረታ መብት አልነበራቸውም፡፡

ያለባቸው የስራ ጫናና የሚከፈላቸው ክፍያ አነስተኛ መሆን ለዚህ የተቃውሞ ሰልፍ ገፍቶ አደባባይ ሲያስወጣቸው ሴቶች በታሪክ በተደራጀ መንገድ ማህበራዊ መብቶቻቸውን ለማስከበር የጠየቁበት ነው። ይህ ከሆነ ከሁለት ዓመት በኋላ በዴንማርክ ኮፐንሃገን በተካሄደው በሁለተኛው አለም አቀፍ የሴቶች ኮንፈረንስ በጀርመናዊቷ ክላራ ዜትኪን ሃሳብ አቅራቢነት 'ማርች 8' አለም አቀፍ የሴቶች ቀን እንዲሆን ተወሰነ፡፡

የኢትዮጵያ ሴቶች ያበረከቱት አኩሪ አስተዋጽዎ በተለያየ አጋጣሚ ቢገለጽም የአገራችን ሴቶች ጉልህ ታሪክ በአግባቡ አልተሰነደም። ሴቶች በበርካታ የሙያ ዘርፎች ከፍተኛ አስተዋጽዎ አስመዝግበዋል፣ እያስመዘገቡም ይገኛሉ። እነ ክላራ ዜትኪን ለሴቶች መብት ለመሟገት ለትግል ከተነሱበት ዘመን አስቀድሞ በኢትዮጵያ ውስጥ ትግል አድርገው የሴቷን መብት ለማስከበር ጥረት ያደረጉበት ሁኔታ እንደነበር ማወቅ ይቻላል። በቅርቡ በብሔራዊ ቲያትር ከመድረክ የወረደው በእውነተኛ ታሪክ ላይ ተመስርቶ የተዘጋጀው 'የቃቄ ወርድወት' ተውኔት የዚህ ማሳያ ነው።

ሴቶች ለኢትዮጵያ አንድነትና ሉዓላዊነት፣ ለሕዝባቸው መብትና ክብር አኩሪ ተጋድሎ አድርገዋል፣ መስዋዕትነትም ከፍለዋል። የካቲት 1966 ዓ.ም. ሕዝባዊ አብዮት “የሴቶችን ጥያቄ” ከፍ በማድረግ ሴቶች ከሚደርስባቸው መደባዊ ጭቆናና ምዝበራ በተጨማሪ በፆታቸው የሚደርስባቸውን በደልና ድርብ ጭቆና ለመታገል መስዋዕትነት ከፍለዋል፣ ማንነታቸውንም አሳይተዋል።

ሴቶች  ከማጀት የዘለለ ሚና እንደሌላቸውና ሚናቸውን በወንዶች ጥገኝነት በመወሰን ዝቅ ብለው እንዲኖሩ ያደረጋቸው የዕምነትና የአጓጉል ባህልና ሥርዓት ጥሎት ያለፈውን አመለካከት ለመቀየር ያላሰለሰሰ ትግል አድርገዋል። የኢትዮጵያ ሴቶች በፖለቲካው መስክ ሚናቸው እየጎላ የመጣው የየካቲት 1966ቱ ግብታዊ አብዮት ጋ ተያይዞ መሆኑ ባይካድም ለዚህ መሠረታቸው ደግሞ አስከፊው ፊውዳላዊ ሥርዓት ያደረሰባቸው ግፍና በደል እንደነበር አይዘነጋም።

በአገሪቱ የፖለቲካ ተሳትፎ ለውጥ እንዲመጣ ከወንዶች ያላነሰ አስተዋጽኦ ቢያበረከቱም ታሪክና ጊዜ ለሴቶች የሰጡት ድርሻ ዝቅተኛ ሆኖ እናገኘዋለን። በአገሪቱ የፖለቲካ ተሳትፎና ውሳኔ ሰጪነትም እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የበዪ ተመልካች ሆነው ቆይተዋል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በ1948 ባወጣው የሰብዓዊ መብት ዝርዝር መግለጫ ላይ የሴቶችን ተሳትፎ በሁሉም ዘርፍ ማሳደግ ማሳደግ እንደሚገባ አመላክቷል።

የመግለጫው አንቀጽ 2 እና 21 ሴቶች በጾታቸው ምክንያት መድልኦ ሳይደረግባቸው የፖለቲካ መብቶቻቸውን እንዲጠቀሙ ደንግጓል፡፡ እአአ በ1966 የወጣው የፖለቲካና የሲቪል መብቶች ቃል ኪዳን ስምምነት በመግለጫው የተጠቀሰውን የሴቶች በመንግሥትና የፖለቲካ ሕይወት ያለምንም መድልኦ የመሳተፍ መብታቸውን አጠናክሮ ደንግጓል፡፡

ሴቶች ወደ ፖለቲካ ውሳኔ ሰጪነት እንዳይመጡ የሚያደርጓቸው ተግዳሮቶች ከአገር አገር ስለሚለያዩ ሰፋ ያለ ጥናት ይፈልጋል፡፡ ከተለያዩ ጥናቶችና ተሞክሮዎች ለመገንዘብ እንደሚቻለው ሴቶች ወደ ፖለቲካ አመራር ሰጪነት እንዳይመጡ የሚያደርጉ ምክንያቶች አሉ፡፡

በአገራችን ነባራዊ ሁኔታ የመጀመሪያው ባህላዊና ኋላቀር አስተሳሰብ ነው፡፡ ሴቶችን ከአደባባይ ሥራ ይልቅ በጓዳ የሚገድብ ባህል ባለበት ሴቶች ከልጆች አስተዳደግ ውጭ ያላቸውን ወይም የሚኖራቸውን ሚና የሚቀበል አሠራር መገንባት አስቸጋሪ ሆኖ ቆይቷል። እንዲህ ዓይነት ባህል በወንድ የበላይነት ላይ የተመሠረተ በመሆኑ የሴቶችን የፖለቲካ ተሳትፎ አይደለም እኩልነታቸው የሚገዳደሩ አስተሳሰቦች ይበዙበታል፡፡ እነዚህ ባህሎች፣ አመለካከቶችና ኋላቀር አስተሳሰቦች ለሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ ተግዳሮት መሆናቸው አይቀርም፡፡

ሁለተኛው ምክንያት ብዙኃኑ ሴቶቹ ለፖለቲካ ተሳትፎ ብቁ የሚያደርጋቸው የትምህርት ሥልጠናና የሥራ ልምድ የሌላቸው መሆኑ፣ ትምህርቱና ልምዱም ቢኖራቸው በፖለቲካ የውሳኔ ሰጪነት ቦታ ለመሳተፍ ፈቃደኛ አለመሆናቸው ነው፡፡ በአገራችን ሴቶች ቁጥራቸው ብዙ ቢሆንም የብዛታቸውን ያህል ትምህርት ያገኙት ጥቂት መሆናቸው ግልጽ ነው፡፡

የፖለቲካ ውሳኔ ሰጪነት ደግሞ ትምህርትና ልምድ ስለሚጠይቅ ሴቶች ተመራጭ ሳይሆኑ የሚቀሩበት አጋጣሚ አለ፡፡ አንዳንዴ ደግሞ ሴቶቹ ብቁ ቢሆኑም፣ ሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎአቸውን ከማጠንከር ይልቅ በማኅበራዊ ሕይወት መሳተፍን ሲያስቀድሙ ይስተዋላል፡፡ ይህ ሌላው ተግዳሮት መሆኑ አልቀረም፡፡

ኢትዮጵያ የሴቶችን ፖለቲካዊ ተሳትፎ ዋስትና የሰጡ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ፈራሚ ከመሆኗ በተጨማሪ የሚሌኒየም ልማት ግብ ለመፈጸም ደፋ ቀና ከሚሉ አገሮች መካከል አንዷ ነች፡፡ በመርህ ደረጃ አገሪቱ ስምምነቶቹን መፈረሟና የልማት ግቦቹን ተቀብላ ለማስፈጸም መትጋቷ በሕግ ደረጃ የሴቶቹን መብት ላለማክበር ክፍተት አለመኖሩን ያሳያል፡፡

አገራችን የጾታ መድሎን ለማስቀረት በተለያዩ ብሔራዊና ክልላዊ ፖሊሲዎች ውስጥ የሴቶችን ጉዳይ እንዲካተት አድርጋለች፡፡ የጾታ እኩልነት በየሴክተሩ መካተቱን ለማረጋገጥ የሴቶች ብሔራዊ ፖሊሲ ተቀርጾ በመፈፀም ላይ ሲሆን፣ ተግባራዊ አፈጻጸሙን ለማጠናከር የጾታ እኩልነት ብሔራዊ የድርጊት መርሃ ግብር ተተግብሯል፡፡

አገሪቱን ለሴቶችና ሕፃናት መብት ያላትን ቁርጠኝነት በሕገ መንግሥቱ ዝርዝር መብቶቻቸውን በማረጋገጥ የገለጸች ሲሆን፣ ሕገ መንግሥቱን መሠረት አድርጎም የቤተሰብ ሕጉና የወንጀል ሕጉ እንዲሻሻል አድርጋለች፡፡ ሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 35 ሴቶች ሕገ መንግሥቱ ባረጋገጣቸው መብቶችና ጥበቃዎች በመጠቀም ረገድ ፖለቲካዊ ተሳትፎን ጨምሮ ከወንዶች ጋር እኩል መብት እንዳላቸው አረጋግጧል፡፡

በተጨማሪም በሕገ መንግሥቱ መሠረት ሴቶች የአዎንታዊ ርምጃ ተጠቃሚዎች እንዲሆኑ የተደነገገ ሲሆን፣ ርምጃው ከሚፈጸምባቸው ሴክተሮች መካከል የፖለቲካው ሴክተር አንዱ መሆኑ በሕገ መንግሥቱ ተደንግጓል፡፡ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድና ብሔራዊ የሰብዓዊ መብት የድርጊት መርሃ ግብር ሴቶች በፖለቲካዊ ተሳትፎአቸው ከወንዶች እኩል ተጠቃሚ የሚሆኑበትን አሠራር አካትተዋል፡፡

ጥቅምት 6 ቀን 2011 ዓ.ም  የህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የቀረቡለትን ሚኒስትሮች ሹመት ሲያፀድቅ ሴቶች ግማሽ ያህሉን ቦታ አግኝተዋል። በዕለቱ በሚኒስትርነት ከተሾሙት መካከል የትራንስፖርት ሚኒስትሯ ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ እንደሚሉት፤ አጠቃላይ የሴቶች ሹመቱ በህግ አውጭው በኩል ነገሮች እየተሻሻሉ ቢመጡም በአስፈፃሚው በኩል ይነሳ የነበረውን ጉድለት በተለይም በከፍተኛ ደረጃዎች ላይ ሴቶችን ማሳተፍን በሚመለከት ያለውን የአፈፃፀም ክፍተት ከመሰረቱ የቀየረና ትልቅ ትርጉም ያለው እርምጃ ነው። የአዲሱን ሹመት ሃምሳ በመቶ ሴቶች ማግኘታቸውን ብዙዎች በተለያየ መንገድ ተመልክተውታል። የሴታዊት መስራች ዶ/ር ስህን ተፈራ "ሃምሳ በመቶ ሹመት ከጠበቅነውና ማንም መጠየቅ ከሚችለው በላይ ነው" ይላሉ።

ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን የዓለም ሴቶች በዓሉን ምክንያት በማድረግ አንድነታቸውን፣ ዓላማቸውንና ተስፋቸውን የሚገልጹበት ዕለት ነው።

የኢትዮጵያ ሴቶችም በረሃብ የሚሰቃዩ፣ ወደ ባዕድ አገር በሽያጭ የሚጓዙ እህቶቻቸው፣ ያለ ዕድሜያቸው ለወሲብ ጥቃትና አስገድዶ መደፈር የሚዲረጉ ሕፃናት፣ ጧሪ ያጡ አረጋውያን እናቶች፣ አሳዳጊ ያጡ ሕፃናት፣ በተለያየ ሕመም በሚሰቃዩ እህቶቻችን ላይ ያሳረፈውን መከራና ጫና በመታገል አንድነታቸውን የሚያጠነክሩበት፣ የወደፊት የትግል አቅጣጫቸውን የሚቀይሱበት፣ የሚያቀነባብሩበትና የትግላቸውን መስመር የሚመረምሩበት ቀን ሊሆን ይገባዋል።

ኢትዮጵያን ወደተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር በሚደረገው ጥረት ላይ ደማቅ አሻራቸውን ማሳረፍ የሚችሉበት ምቹ ሁኔታ ዛሬ ላይ መፈጠሩን መገንዘብ ይቻላል። ከቀደመው ትውልድ የተወረሰውን ነጻነትና አንድነት ለማስቀጠል የጎላ ሚና እየተጫወቱ ይገኛል። በቀጣይም የተሻለ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ። 'ማርች 8' በኢትዮጵያ ሲከበር ዛሬ እየደመቀ ለመጣው ብርሃን መሰረት የጣሉ ቀደምት ኢትዮጵያውያን ሴቶች ተገቢውን ዕውቅና በመስጠት ሊሆን ይገባል።

'ማርች 8' ኢትዮጵያውያን በዘርና በሃይማኖት ያልተከፋፈለች ኢትዮጵያ ዳግም ትንሳዔዋ ይሆን ዘንድ ወገባቸውን ጠበቅ የሚያደርጉበት የትግል ቀን ናት። 'ማርች 8' ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀንን ሲታወስ የሴቶችን የትግል ታሪክ ለቀጣይ ትውልድ ትምህርት ይሆን ዘንድ በማስገንዘብ ነው።

ከዚህ በፊት ከነበሩ ቀደምት ሴት ታጋዮች ጠንካራና ደካማ ጎን ትምህርት በመቅሰም ኢትዮጵያን የሁሉም ዜጎች እኩል ቤት እንድትሆን ማድረግ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም