አንድነታቸውን በማጠናከር ታሪካዊ ቅርሶችን ለመጠበቅ የድርሻቸውን እንደሚወጡ በሐረሪ ክልል ነዋሪዎች ገለጹ

97

ሐረር የካቲት 27/2011 የአካባቢያቸውን ሰላምና አንድነታቸውን በማጠናከር  ታሪካዊ ቅርሶች ጠብቆ ለትውልድ ለማስተላለፍ የድርሻቸውን እንደሚወጡ በሐረሪ ክልል  ነዋሪዎች ገለጹ።

" ጉዞ ሉሲ ለሰላምና ለፍቅር " በሚል ሐረሪ የደረሰው የሉሲ ቅሪተ አካል ምክንያት በማድረግ የተዘጋጀ  አውደ ርዕይ በክልሉ ነዋሪዎች እየተጎበኘ ነው።

ኢዜአ ያነጋገራቸው ጎብኚዎች እንዳሉት  የሉሲ ቅሪተ አካል ወደ ክልሉ መምጣቱ ወጣቱ የራሱ የሆኑ መገለጫ ቅርሶችን ለመጠበቅና አንድነትን ለማጠናከር ያግዛል፡፡

አቶ ኤልያስ ፈቲ ከጎብኚዎቹ ውስጥ አንዱ ሲሆኑ " ኢትዮጵያዊያን በአንድነትና በነጻነት የኖርን እና የበርካታ ቅርስ ባለቤት ነን ፤  ሆኖም  ከቅርብ ጊዜ ወዲህ  ይህንን አኩሪ ታሪካችንን የማበላሸት እንቅስቃሴ እየተስተዋለ ይገኛል" ሲል በሰጡት አስተያየት ተናግረዋል።

መልካም እሴቶችን የሚያጎድፉ እንቅሰቃሴዎችን ህብረተሰቡ በነቃ ተሳትፎ በመታገል የመቻቻልና የመረዳዳት ባህልን  ማጎልበት ከሁሉም እንደሚጠበቅ አመልክተዋል።

" የሉሲን ቅሪተ አካል መመልከት ችያለው፤ ይህም ታሪኬንና አመጣጤን እንድረዳ አስችሎኛል" ያለው ደግሞ ወጣት ታሪኩ ገለታ ነው፡፡

የቅሪተ አካሉ ወደ ሐረሪ መምጣት  አለመግባባቶች ለመፍታት ፣ሰላምና አንድነትን ለማጎልበት እንደሚያግዝ ገልፆ እሱም  ታሪካዊ ቅርሶችን ጠብቆ ለመጪው ትውልድ ለማስተላለፍ የድርሻውን እንዲወጣ ያነሳሰው መሆኑን ተናግሯል፡፡

ወይዘሪት ፈርዶሳ አቡበከር በበኩላቸው የሉሲ ቅሪተ አካል ወደ ክልሉ መምጣት የክልሉ ገጽታ የሆነው የመቻቻልና አብሮ የመኖር እሴትን ለመጠበቅ  የበኩሉን አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ገልጸዋል።

" ቅሪተ አካሉ ወደ ክልሉ ሲመጣ እኛ ሴቶች ላይ የተለየ ደስታ ፈጥሮብናል፤ በክልሉ የሚስተዋሉ አለመግባባቶን ከአገር ሽማግሌዎችና ከኃይማኖት አባቶች ጋር በመፍታት መልካም እሴቶች እንድንጠብቅ ያበረታታናል" ብለዋል።

የሉሲ ቅሪተ አካል ነዋሪው በሰላምና በአንድነት ላይ ያለው ግንዛቤው እንዲጎለብት፣ የመቻቻልና የአብሮነት ባህል እንዲጠናከር እድል እየፈጠረ ይገኛል"ያሉት ደግሞ የክልሉ ባህል፣ቱሪዝምና ቅርስ ቢሮ ኃላፊ አቶ ዲኒ ረመዳን  ናቸው።

ሐረር የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች የሚኖሩባት፣ የተለያዩ ቋንቋዎች የሚነገሩባት፣ሙዚየሞችና የመስህብ ስፍራዎች የሚገኙባት  የሰላምና የመቻቻል ክልል መሆኑን አስታውሰው  ወጣቱም ይህን ታሪክ በአንድነት ሊንከባከበውና ሊጠብቀው እንደሚገባ አሳስበዋል።

በአሚር አብዱላሂ መሰብሰቢያ አዳራሽ የተዘጋጀውን አውደ ርዕይ አሁንም በመቀጠል በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ሐረር ከተማ በሚገኘው ጤናና ህክምና ሳይንስ ኮሌጅ ተማሪዎች፣ መምህራንና የአካባቢው ማህበረሰብ እየተጎበኘ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም