ለህዝብና ቤቶች ቆጠራ ስኬታማነት ሁሉም በኃላፊነት ሊንቀሳቀስ እንደሚገባ ተጠቆመ

619

ጋምቤላ መቀሌ/ሚዛን/  የካቲት 27/2011 በሀገር አቀፍ ደረጃ ለአራተኛ ጊዜ የሚካሄደው የህዝብና የቤቶች ቆጠራ በጋምቤላ ክልል ስኬታማ እንዲሆን በቆጠራው የሚሳተፉ አካላት ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አሳሰቡ፡፡

በክልሉ ለሚካሄደው የህዝብና ቤቶች ቆጠራ የሚሳተፉ የአሰልጣኞች ሥልጠና ትናንት በጋምቤላ ከተማ ተጀምሯል፡፡

በስልጠናው ላይ የተገኙት የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት በክልሉ ብሎም በሀገሪቱ ለአራተኛ ጊዜ የሚካሄደውን የህዝብና ቤት ቆጠራ የተሳካ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ ነው፡፡

በቆጠራው የሚሰበሰበው መረጃ ለመጪዎቹ አስር ዓመታት ለክልሉ ህዝብ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ወሳኝ በመሆኑ በቆጠራው የሚሳተፉ አካላት  ትክክለኛና ተአማኒነት ያለውን መረጃ በመሰብሰብ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ አሳስበዋል።

የክልሉ መንግስት የህዝብና ቤት ቆጠራውን ውጤታማ ለማድረግ በየደረጃው የሚገኙ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ኡሞድ ቆጠራውን በበላይነት የሚመሩ አካላት ከክልል እስከ ታችኛው የአስተዳደር እርከን ድረስ መዋቀራቸውን ተናግረዋል፡፡

የክልሉ ህዝብም ለቆጠራ ሥራው ስኬታማነት አስፈላጊውን መረጃ ለቆጣሪዎች በመስጠት የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

በማዕከላዊ ስታስቲክስ ኤጀንሲ የጋምቤላ ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ አቶ ዱባለ ከበደ በበኩላቸው “የህዝብና ቤት ቆጠራው በክልሉ ብሎም በሀገሪቱ የወሳኝ ኩነቶችን መረጃ ከመስጠት ባለፈ ለመሰረተ ልማት ዝርጋታ አስፈላጊ ነው” ብለዋል፡፡

ለአራተኛ ጊዜ ለሚካሄደው የህዝብና ቤት ቆጠራ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቱ ዝግጅት ማጠናቀቁንና በአሁኑ ወቅትም በቆጠራው ተሳታፊ የሚሆኑ የአሰልጣኞች ሥልጠና መጀመሩን ተናግረዋል፡፡

በተመሳሳይ ዜና ከተለያዩ የትግራይ ወረዳዎች ለመጡ የህዝብና ቤቶች ቆጠራ ሥራ ተሳታፊ ባለሙያዎች የአሰልጣኞ ስልጠና ከትናንት ጀምሮ እየተሰጠ ነው።

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የንግድ ኢንዱስቱሪና ከተማ ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር አብርሃም ተከስተ በእዚህ ወቅት እንዳሉት የህዝብና ቤቶች  ቆጠራ በተሳካ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ ሁሉም በኃላፊነት መንፈስ ሊሰራ ይገባል፡፡

“በቆጠራ ሥራ የሚሳተፉ ሰልጣኞችም በትኩረትና በንቃት በመንቀሳቀስ ስራውን በእውቀት መምራትና ለሌሎች ማስተማር ይኖርባቸዋል” ብለዋል፡፡

ቆጣሪዎችና ተቆጣጣሪዎች ፈታኝ ነገሮች ቢገጥማቸውም ተቋቁመው ሁሉንም ሰውና ቤት በአግባቡ በመቁጠር ኃላፊነታቸውን እንዲወጡም አመልክተዋል።

የመቀሌ ስታስቲክስ ባለስልጣን ኃላፊና የቆጠራው ኮሚሽን ጸሐፊ አቶ አማረ ገብረዋህድ በበኩላቸው በስልጠናው ከተለያዩ ወረዳዎች የመጡ 534 ሰልጣኞች በመሳተፍ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የዘንድሮ ቆጠራ በቴክኖሎጂና በታብሌት ሞባይል የታገዘ መሆኑ ቀደም ካሉት ቆጠራዎች እንደሚለየው ጠቁመው ሰልጣኞቹ ከቴክኖሎጂው ጋር እንዲተዋወቁ የንድፍ ሃሳብና የተግባር ስልጠና እንደሚሰጣቸው ገልጸዋል፡፡

በአሰልጣኞች ስልጠና እየተሳተፉ ካሉት መካከል የስታስቲክስ ባለሙያ አቶ ሐዱሽ አርአያ እንዳሉት ስልጠናው ከቴክኖሎጂ ጋር የተያያዘ በመሆኑ ስህተቶች እንዳይከሰቱ ያግዛል፡፡

“በገጠራማ አካባቢዎች ከመንገድ አለመመቸትና ከቤቶች ተራርቆ መገኘት ጋር በተያያዘ ሥራው አድካሚ ቢሆንም በተሰጠን ስልጠና መሰረት ኃላፊነቴን በአግባቡ እወጣለሁ ’’ ብለዋል።

በተመሳሳይ ከካፋ፣ ሸካ፣ ቤንች ማጂና የም ልዩ ወረዳ ለተውጣጡና በሕዝብና ቤት ቆጠራ ሥራ ለሚሳተፉ በሚዛን ከተማ የአሰልጣኞች ስልጠና  እየተሰጠ ነው።

በስልጠናው መክፈቻ ላይ የተገኙት የቤንች ማጂ ዞን አስተዳደር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኤፍሬም ጢሞቲዎስ በሕዝብና ቤት ቆጠራው የሚሰማሩ ባለሙያዎችና ባለድርሻ አካላት ቆጠራው ስኬታማ እንዲሆን ሀገራዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።

“ትክክለኛ የሕዝብ ቁጥርን ማወቅ አስተማማኝ ሀገራዊ ዕቅድና ስትራቴጂ ለመንደፍ ያስችላል” ያሉት አቶ ኤፍሬም የዞኑ አስተዳደር ቆጠራው እስኪጠናቀቅ ድረስ ድጋፉን እንደሚያጠናክር አረጋግጠዋል።

የሕዝብና ቤቶች ቆጠራው የተሳካ እንዲሆን ከወዲሁ በቂ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የሚዛን ስታስቲክስ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ስራ አስፈጻሚ አቶ አማኑኤል አንጁሎ ናቸው።

እሳቸው እንዳሉት ከካፋ፣ ሸካ፣ ቤንች ማጂ ዞኖችና በየም ልዩ ወረዳ 3 ሺህ 766 የቆጠራ ቦታዎችና 998 መቆጣጠሪያ ጣቢያዎች ተለይተው ተዘጋጅተዋል።

በቆጠራ ሂደቱ ችግር ከተፈጠረ መፍትሄ መስጠት የሚችሉ 34 የአይሲቲ ባለሙያዎች ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ትናንት በጋምቤላ፣ መቀሌና ሚዛን ከተሞች የተጀመረው የአሰልጣኞች ስልጠና ለሁለት ሳምንት እንደሚቆይ ታውቋል።