በንግድ እንቅስቃሴያቸው ተጽዕኖ የሚያሳድሩ ችግሮች እንዲፈቱላቸው የትግራይ ደቡባዊ ዞን ነጋዴዎች ጠየቁ

61

ማይጨው የካቲት 27/2011 በንግድ እንቅስቃሴያቸው ተጽዕኖ የሚያሳድሩባቸው የሕገ ወጥ ንግድ መስፋፋትና የአሰራር ችግሮች እንዲቀረፉላቸው በትግራይ የደቡባዊ ዞን የንግድ ማህበረሰብ አባላት ጠየቁ።

በዞኑ በተለያዩ የንግድ ዘርፎች የተሰማሩ ከ500 በላይ የንግድ ማህበረሰብ አባላት በዘርፉ ላይ ያተኮረ ስብሰባ በአላማጣ ከተማ አካሄደዋል።

በመሆኒ ከተማ በንግድ ሥራ የሚተዳደሩት  አቶ ንጉስ ከበደ የሕገ ወጥ ንግድ መስፋፋት በግብር ከፋይ ነጋዴዎች ገቢ ጫና እያሳደረ ነው፡፡

በከተማው ንግድ ፈቃድ የሌላቸው በሸቀጣ ሸቀጥ፣ በቁርስና ምግብ ቤት መስኮች የሚሰሩ ሕገ ወጥ ነጋዴዎች መበራከታቸውን ጠቁመዋል።

ከሌሎች አካባቢዎች በጭነት ተሽከርካሪዎች የሚመጡ የታሸገ መጠጥ፣ ውሃና ፈሳሽ ሳሙና በጅምላ ነጋዴዎች ገቢ ላይ ተጽዕኖ እያሳረፉ ናቸው  ብለዋል።

የትግራይ ክልል ገቢዎች ባለሥልጣን ሠራተኞች ግብር ከከፈሉ በኋላ ቀሪ ግብር የሚጠይቁበት አሰራር እንዲስተካክላቸው የጠየቁት በኮረም ከተማ በኮንስትራክሽን ዘርፍ የተሰማሩት አቶ ደሞዝ ዋሲሁን ናቸው፡፡

''ነጋዴው ግብር መክፈል ያለበት በወቅቱ ነው'' ያሉት አስተያየት ሰጪው፣ ''ከዚህ ውጭ ግብር ከከፈልንና ንግድ ፈቃዳችን ከታደሰ ከአንድ ዓመት በኋላ ውዝፍ ግብር  መጠየቅ ተገቢነት የለውም'' ብለዋል፡፡

የኮረም ከተማ ነጋዴው  አቶ ሞላ ባቤ በሰጡት አስተያየት የክልሉ ዋና ኦዲተር ሠራተኞች የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የሂሳብ ምርመራ ከማድረግ ውጭ የነጋዴዎችን የሂሳብ መዝገብ መፈተሻቸው ሊታረም እንደሚገባው ይናገራሉ።

አሰራሩ ካልተወገደ ከንግዱ ማህበረሰብ ጋር የሚፈጠረው ግንኙነት ለሙስና በር በመክፈት ገቢ አሰባሰቡን እየጎዳው መሆኑን አስረድተዋል፡፡

''ደረሰኝ አልቆረጥክም ተብዬ የ50 ሺህ ብር ቅጣት ተጥሎብኝ ይግባኝ ብጠይቅም ሰሚ አጥቻለሁ'' ያሉት ደግሞ በማይጨው ከተማ በንግድ ሥራ የሚተዳደሩት አቶ ሐጎስ ወልደስላሴ ናቸው፡፡

መንግሥት ከደረሰኝ ጋር ተያይዞ  የሚታየውን ክፍተት ለመሸፈን ሥልጠና ሊሰጣቸው እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

ደረሰኝ አልቆረጥክም ተብለው  ከአንድ ዓመት በኋላ  በሂሳብ ምርመራ ለተገኘው ስህተታቸው መቀጣታቸው አግባብ እንዳልሆነ አቶ ሐጎስ ተናግረዋል፡፡

የትግራይ ደቡባዊ ዞን ንግድና ከተማ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ አስመላሽ ረዳ በገቢ አሰባሰብ ረገድ የሚታዩ ችግሮች የአስፈፃሚ አካላትና የንግዱ ማህበረሰብ አባላት ተቀናጅተው ያለመስራታቸው ውጤት መሆኑን ያስረዳሉ፡፡

የንግዱ ማህበረሰብ ከውዝፍ ግብር ጋር በወቅቱ እንዲከፍል አለመደረጉን አስመልክቶ ያቀረበው ቅሬታ ተገቢ መሆኑ ገልጸው፣

አሰባሰቡን በቴክኖሎጂ በተደገፈ አሰራር በመተካት ግሩን ለማቃለል እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

የንግዱ ማህበረሰብ የሂሳብ መዝገብ ምርመራ በዋና ኦዲተር ሠራተኞች ሳይሆን፤ በወረዳዎቹ የገቢዎች ጽህፈት ቤቶች ባለሙያዎች ኦዲት ይደረጋል ሲሉም አስታውቀዋል።

የተጨማሪ እሴት ታክስ /የቫት/ ገንዘብ የማያስገቡና ደረሰኝ የማይቆርጡ ነጋዴዎች ግን ቅጣት እንደሚጣልባቸው ኃላፊው ገልጸዋል፡፡

ሕገወጥ ንግድ የመንግሥትን ገቢ ስለሚያሳጣ ሥርዓት ማስያዝ እንደሚገባ አመልክተዋል።

የትግራይ ገቢዎች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ አሰፉ ሊላይ እንዳሉት የክልሉ የመንግሥት ገቢ አሰባሰብ ላይ በየዓመቱ ዕድገት ቢያሳይም፤ አፈፃፀሙ ግን ከሚፈለገው በታች ነው፡፡

በደቡባዊ ዞን በ2010 ከቀዳሚው ዓመት 225 ሚሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡን ተናግረዋል፡፡ ይህም ከዕቅዱ በ36 ሚሊዮን ብር ብልጫ ነበረው።

ገቢው ለዞኑ ልማት ፕሮጀክቶች በየዓመቱ ከሚመድበው በጀት 21 በመቶ እንደሚሸፍን ገልጸዋል፡፡

በክልል ደረጃም ከንግዱ ዘርፍ የሚገኘው ገቢ መንግሥት ለልማት ከሚመድበው በጀት ጋር ሲነጻጸር 35 በመቶ ብቻ እንደሚሸፍን ወይዘሮ አሰፉ ገልጸዋል፡፡

የሕገ ወጥ ንግድ መስፋፋትና ለተጨማሪ እሴት ታክስ የተሰበሰበውን ገቢ ለግል ጥቅም ማዋል ዋነኛ ችግሮች መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡

ደረሰኝ ያለመቁረጥ፣ሐሰተኛ ደረሰኝ በማዘጋጀት በአቋራጭ ለመበልጸግ መሻት፣ ግብር ስወራና ማጭበርበር ገቢ በአግባቡ እንዳይሰበሰብ የሚያደርጉ ምክንያቶች ናቸው ብለዋል፡፡

ገቢን በማሳደግ የድህነትንና የሥራ አጥነትን ችግሮችን መቀነስ እንደሚሻ ያመለከቱት ወይዘሮ አሰፉ፣የንግዱ ማህበረሰብ አባላት ግዴታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም