ማዕከሉ ፕሮሶፒስ የተባለው መጤ አረም ለማስወገድ መፍትሔ ማግኘቱን አስታወቀ

131

አዳማ የካቲት 27/2011 የወረር ግብርና ምርምር ማዕከል በአፋር ክልል አንድ ሚሊዮን 300ሺህ ሄክታር  የተፈጥሮ የሳር ግጦሽ መሬትን  የወረረው ፕሮሶፒስ ጁሊፍሎራ  የተባለው መጤ አረም ለማስወገድ የሚያስችል መፍትሔ ማግኘቱን አስታወቀ ።

መጤ  አረሙ የተፈጥሮ ግጦሽ መሬትን  በመውረር አርብቶ አደሩን ለችግር ሲያጋልጥ ቆይቷል ።

የማዕከሉ ተወካይ አቶ አሸናፊ ወርቁ ለኢዜአ እንደተናገሩት  አረሙ በ1970ዎቹ መጀመሪያ በረሃማነትን ለመከላከል፣  እርሻዎችን ከአባሯና ከአውሬ ለመጠበቅ እንደ አጥር ያገለግላል ተብሎ ወደ ሀገር  የገባ ነው።

በሂደት በአሳሳቢ ሁኔታ በመስፋፋት በአፋር  አንድ ሚሊዮን 300ሺህ ሄክታር  ፣በአጎራባች የኦሮሚያ አካባቢዎች ፣በድሬዳዋና በሶማሌ ክልል ደግሞ ሰፊ የተፈጥሮ ግጦሽ መሬቶችን ወሯል፡፡

ይህም ብዝሃ ህይወትን በማጥፋት አርብቶ አደሩን በቀላሉ ለድርቅ ተጋላጭ እንዲሆን ማድረጉን የምርምር ማዕከሉ ተወካይ ተናግረዋል ።

በየደረጃው የሚገኙ  የመስተዳድር መዋቅሮችና ጉዳዩ የሚመለከታቸው ሌሎች ባለድርሻ አካላት የመጤ አረሙን አሳሳቢነት በመገንዘብ በጋራና በተናጠል ለማጥፋት ያደረጉት ጥረት ሳይሳካ መቆየቱንም  አስረድተዋል ።

የኋላ ኋላ የተሻለ አማራጭ ሆኖ የተገኘው አረሙ በሰው ጉልበት እየተነቀለ እንዲቃጠል ማድረግ  ቢሆንም በጊዜ ፣ በጉልበትና በወጪ ደረጃ አዋጪ ሆኖ አልተገኘም ።

የምርምር ማዕከሉ አማራጭ ቴክኖሎጂዎችን በማፈላለግ ካቪ ከተባለ ዓለም አቀፍ የምርምር ተቋም  ጋር በመተባበር ከደቡብ አፍሪካ ሁለት   የኬሚካል ዓይነቶችን በማስመጣት ባለፉት ዓመታት በተግባር በመሞከር ውጤታማ መሆናቸውን አቶ አሸናፊ  አረጋግጧል ።

በአንድ ሄክታር መሬት የሚገኝ ፕሮሶፒስ ጁሊፍሎራ አረም በሰው ጉልበት ለመንቀል  እስከ 30 የሚደርሱ ሰዎች በማሰማራት እስከ አራት ቀናት እንደሚወስድ ገልጸው በኬሚካሎቹ ግን በቀን አንድ ሰው እስከ አምስት ሔክታር ማዳረስ እንደሚቻል ጠቅሰዋል።

ከወጪ አንፃርም ቢሆን በሰው ጉልበት አረሙን ከአንድ ሔክታር ለማስወገድ እስከ 13 ሺህ ብር እንደሚጠይቅና በ12 ዶላር በሚገዛ ኬሚካል ግን አምስት ሔክታር መሬት ከአረሙ ነፃ ማድረግ እንደሚቻል  አስረድተዋል ።

አንደኛው ኬሚካል የወራሪው አረም ስር እስከ 15 ሳንቲሜትር ከፍታ  ድረስ በመርጨት ፣ ሁለተኛው ኬሚካል ደግሞ አረሙን ከታች ቆርጦ በመቀባት በቀላሉ ማስወገድ እንደሚቻል በተግባር ተረጋግጧል ።

ኬሚካሎቹ አረሙን በመጀመሪያው አምስት ቀናት ቢጫ መልክ እንዲይዝና  በ15 ቀናት ውስጥ ደግሞ በማድረቅ እንዲጠፋ የማድረግ አቅም እንዳላቸው አቶ አሸናፊ ተናግረዋል፡፡

አረሙ በእንስሳት ሀብቶቻቸው ላይ ጉዳት ካደረሰባቸው የአፋር ክልል ነዋሪዎች መካከል በአሚባራ ወረዳ የወረር አካባቢ  አርብቶ አደር መሐመድ ሁሴን አንቱታ አንዱ ናቸው፡፡

እሳቸው እንዳሉት መጤ ወራሪው  አረም በአካባቢያቸው የነበረው የግጦሽ ሳርና ለመኖነት የሚያገለግሉ እፅዋቶች በሙሉ አጥፍቶባቸዋል።

ከዚህም ባሻገር የአረሙ እሾህ የቤት እንሰሳትን በመውጋት ዓይናቸው እንዲጠፋ ፣ እግራቸውን በመውጋት እንዲያነክሱና መንጋጋቸው እንዲጣመም በማድረግ ጉዳት እየደረሰባቸው መሆኑን ገልፀዋል ።

የወረር ግብርና ምርምር ማዕከል አሁን የጀመረው አረሙን በኬሚካል የማጥፋት ስራ አጠናክሮ እንዲቀጥልም አርብቶ አደሩ ጠይቀዋል፡፡

የአፋርዋ ሴት አርብቶ አደር ፋጡማ ዓሊ  በበኩላቸው መጤው  አረም በቅርቡ 15 በግና ፍየሎች እንደገደለባቸው አስታውሰው  ኬሚካሉ በስፋት ጥቅም ላይ እንዲውል የሚፈልጉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ከኢትዮጵያ ብዝሃ ህይወት ኢንስቲትዩት የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ   35 አዲስ ወራሪ መጤ የአረም ዝሪያዎች ይገኛሉ ።

በሚያስከትሉት ተፅዕኖ መጠን ክትትል ፣ ቁጥጥርና የማስወገድ ልዩ ትኩረት የተሰጣቸው አራቱ ዋና ዋና መጤ ወራሪ አረሞች ደግሞ ፈረምሲሳ ፣ ፕሮሶፒስ ፣ እምቦጭና የወፍ ቆሎ ናቸው ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም