በትግራይ ሰሜናዊ ምዕራብ ዞን የሙዝ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሰራ ነው

285

ሽሬ እንዳስላሴ የካቲት 27/2011በትግራይ ሰሜናዊ ምዕራብ ዞን የሙዝ ምርትና ምርታማነትን በምርምር ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ቢሮ አስታወቀ።

ቢሮው ከትግራይ ባዮ ቴክኖሎጂ ማዕከል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ጋር በመተባበር የሙዝን ምርት ለማሳደግ የሚያስችል የምርምር ሥራ እያከናወነ መሆኑን አስታውቋል።

የቢሮው ኃላፊ ዶክተር ፀጋ ብርሃነ እንዳሉት የምርምር ሥራው እየተከናወነ ያለው በትግራይ ሰሜናዊ ምዕራብ ዞን የተከዜ ወንዝ ተጠቅመው በሙዝ እያለሙ ባሉ አርሶ አደሮች ማሳ ላይ ነው።

ምርምሩ ቀጣይነት ያለውና የሙዝ ምርትን በጥራትም ይሁን በብዛት ለማምረት የሚያስችል መሆኑን ጠቁመዋል፡

ላለፉት ስምንት ወራት በተካሄደው የምርምር ሥራ “ግራንድ ናይን” እና “ጃይንት ካቨንድሽ” የተባሉ የሙዝ ተክሎች በቂ ምርት እንደሚሰጡ መረጋገጡን የገለጹት ደግሞ በትግራይ ባዮ ቴክኖሎጂ ማዕከል ተመራማሪ አቶ ፀሐየ ቅዱስ ናቸው፡፡

እንደእርሳቸው ገለጻ በሙዝ ምርት የተሰማሩት አርሶ አደሮች በልምድ እያለሙት ያለው “ጫልዳ” የተባለ የሙዝ ተክል ከአንድ የሙዝ ግንድ 150 የሙዝ ዘላለ (ፍሬ) የሚሰጥ ነው፡፡

ግራንድ ናይን እና ጃይንት ካቨንድሽ የተባሉ የሙዝ ዝርያዎች ከአንድ የሙዝ ግንድ እስከ 308 የሙዝ ዘለላ መስጠት የሚችሉ መሆናቸውን ተመራማሪው ተናግረዋል፡፡

“የተሻለ ምርት መስጠት እንደሚችሉ በምርምር የተለዩት እነዚህ የሙዝ ተክሎች በስምንት ወር ውስጥ ለምግብነት የሚደርሱ ከመሆናቸው በተጨማሪ ቀለማቸው ሳቢና ጣፋጭ ናቸው” ብለዋል፡፡

በቀላሉ በበሽታ የማይጠቁና በነፋስ ግፊት የማይወድቁ መሆናቸውን ተመራጭ እንደሚያደርጋቸው ተመራማሪው አመልክተዋል፡፡

በዞኑ በሙዝ ልማት ከተሰማሩ አርሶ አደሮች መካከል አርሶ አደር ደሳለኝ ገብረስላሴ በበኩላቸው በተለምዶ ከሚያለሙት የሙዝ ተክል አሁን የተከሏቸው ግራንድ ናይን እና ጃይንት ካቨንድሽ የሙዝ ዝርያዎች የተሻሉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

“በእኔ ማሳ ለሙከራ ከተተከሉት ሃያ የሙዝ ችግኞች መካከል16 በጥሩ የምርት ሂደት ላይ ናቸው”  ሲሉም ገልጸዋል፡፡

በአሁ ወቅት የሚያለሙት የሙዝ ዝርያዎች ቀደም ሲል ከሚያለሙት ጫልዳ የተባለ የሙዝ ተክል ጋር ሰነጻጸሩ በአንድ ግንድ በሚሰጡት ፍሬ ከአምሳ እስከ ሰማንያ ብልጫ እንዳለውም ተናግረዋል፡፡

በምርምር የተለዩት የሙዝ ተክሎች በብዛት ፈልተው ለአርሶ አደሩ በበቂ ሁኔታ እንዲቀርቡ የጠየቁት ደግሞ በሙዝ ምርት የተሰማሩ አርሶ አደር ሐጎስ ኪዳነ ናቸው።

ሌላው የተሻሻለ የሙዝ ተክል ተጠቃሚ የሆኑት አርሶ አደር መንግስቱ ተክለሃይማኖት በበኩላቸው ለበርካታ ዓመታት ጫልዳ የተባለ የሙዝ ዝርያ ሲያለሙ መቆየታቸውን ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የተከሉት ግራንድ ናይን የተባለው ምርጥ የሙዝ ዝርያ በአንድ የሙዝ ግንድ ከ300 በላይ የሙዝ ፍሬ ማፍራቱን ተናግረዋል፡፡

አዲሱ የሙዝ ዝርያ በምርታማነቱ የተሻለ በመሆኑ በአንድ ጥማድ መሬታቸው ላይ ያለውን ጫልዳ የተባለ የሙዝ ዝርያ አስወግደው በተሻለው ለመተካት መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል፡፡

የተከዜ ወንዝን ተጠቅመው በሙዝ ልማት የተሰማሩ ባለሃብት አቶ ሱራፌል ገብረህይወት በበኩላቸው የተሻሻለና ከቀድሞው በእጥፍ ምርት የሚሰጥ አዲስ የሙዝ ተክል ማግኘታቸው ምርታማነታቸውን ከፍ እንደሚያደርገው ተናግረዋል፡፡

የተሻለ ምርት የሚሰጡት የሙዝ ተክል ችግኞች በብዛት ተዘጋጅተው እንዲቀርቡላቸው ጥያቄ ማቅረባቸውንም ገልጸዋል፡፡

በዞኑ በአስገደ ጽምብላላና በታህታይ አዲያቦ ወረዳዎች የተከዜን ወንዝ በመጠቀም በባለሀብቶችና በአርሶ አደሮች ከ1 ሺህ 5 ሄክታር በላይ መሬት በሙዝ ተክል እየለማ መሆኑን ታውቋል ።