የመላው ኢትዮጵያ ስፖርታዊ የሴቶች ጨዋታ የፊታችን ሐሙስ በጅግጅጋ ይጀመራል

89

በሶማሌ ክልል  አዘጋጅነት የሚካሄደው ሦስተኛው የመላ ኢትዮጵያ የሴቶች ጨዋታ ከነገ በስቲያ በጅግጅጋ ከተማ እንደሚጀመር ተገለጸ፡፡

በጨዋታ ተካፋይ ለመሆን እስካሁን  ስድስት ክልሎችን የሚውክሉ ስፖርተኞች ጅግጅጋ ከተማ  ገብተዋል።

ከገቡት ስፖርተኞች መካከል የኦሮሚያ ፣ የደቡብና የጋምቤላ ይገኙበታል፡፡

ለስፖርተኞቹ ከጅግጅጋ  አስር ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከሚገኘው ሀዳው ከተማ ጀምሮ የአካባቢው ስፖርት ቤተሰቦች አቀባበል እያደረጉላቸው  ነው።

የክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አህመድ ሐሰን እንደገለጹት በጨዋታው  ከ2 ሺህ 500 ያላነሱ ሴት ስፖርተኞች እንደሚሳተፉ ይጠበቃል፡፡

ከፌዴራል ስፖርት ኮሚሽንና  ከኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ጋር በመተባበር  ላዘጋጁት ውድድር ማካሄጃ የጅግጅጋ መለስተኛ ስታዲዮም  የእድሳት ስራ በሁለት ሚሊዮን 200 ሺህ ብር ወጪ መጠናቀቁን አስታውቀዋል፡፡

" ስታዲየሙ እግር ኳስና አትሌቲክስ  ውድድሮች ያስተናግዳል " ያለው ምክትል ኃላፊው ሌሎች የስፖርት ዓይነቶች ደግሞ በ" ሃቫና" የስፖርት ማዕከል እንደሚካሄዱ ተናግረዋል።

ክልሉ ሶስተኛውን የመላ ኢትዮጵያ የሴቶች ጨዋታ በብቃት ለማስተናገድ የውድድር ስፍራዎች ዝግጅት እና የእንግዶች ማረፊያ ቦታዎች ከተለያዩ ተቋማት ጋር በመተባበር ማዘጋጀቱን ገልጸዋል።

በውድድሮቹ ላይ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ  የክልሉ ተወካዮች መዘጋጀታቸውን አመልክተው ጨዋታዎቹ በስፖርቱ ተሰጥኦ ያላቸው ሴቶች ራሳቸውን የሚያሳዩበትና በሌሎች  ውድድሮች ለመሳተፍ እድል የሚያገኙበት እንደሆነም አስረድተዋል፡፡

" የመላ ኢትዮጵያ የሴቶች ጨዋታ ዋና ዓላማ ሴቶች በስፖርተ በማቀራረብ በአካልና በአዕምሮ ንቁና ውጤታማ ሴቶችን መፍጠር ነው" ብለዋል።

ከየካቲት 28 እስከ መጋቢት 8/2011ዓ.ም. ከሚካሄዱት ጨዋታዎች መካከል እግር ኳስ፣ ቦሊቦል፣ ቅርጫርት ኳስ፣ ገመድ ጉተታና አትሌቲክስ የሚገኙበት ሲሆን መሪ ሀሳቡም " ስፖርት ለሴቶች ሁለንተናዊ ለውጥ"  በሚል መሆኑን ሪፖርተራችን ከስፍራው ዘግቧል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም