በደብረ ብርሃን ሪፈራል ሆስፒታል የሚወለዱ ሕፃናት የልደት ምስክር ወረቀት ለማግኘት እየተቸገሩ ነው

624

ደብረ ብርሃን የካቲት 25/2011 በደብረ ብርሃን ሪፈራል ሆስፒታል የሚወለዱ ሕጻናት በወሳኝ ኩነት ቅጽ ስለማይመዘገቡ የልደት ምስክር ወረቀት ለማግኘት እንደሚቸገሩ  የከተማዋና አካባቢዋ ነዋሪዎች ገለጹ።

ሆስፒታሉ ቅጹ ውስጥ ያልተመዘገቡ ሕጻናትን ከባሀር መዝገብ አጣርቼ ለወላዶች እሰጣለሁ ይላል።

ከነዋሪዎቹ የቀበሌ 08 ነዋሪው አቶ ቻላቸው ገረመው ባለቤታቸው በሆስፒታሉ የወሊድ አገልግሎት  ሲሰጣቸው ሕጻኑ በወሳኝ ኩነት ቅጽ ስላልተመዘገበ፤ ከቀበሌያቸው ለሕፃኑ የልደት ምስክር ወረቀት ለማግኘት እንደተቸገሩ አስታውቀዋል፡፡

ወይዘሮ ውዴ ሲሻህ የተባሉ የከተማውነዋሪ በበኩላቸው በሆስፒታሉ ከዘጠኝ ወራት በፊት ለተገላገሉት ልጃቸው በቅጹ ባለመመዝገቡ የልደት ምስክር ወረቀት አለማግኘቱን ይናገራሉ።

ሌላዋ የከተማው ነዋሪ ወይዘሮ መቅደስ ሙሉጌታ ሕፃናቱ የመጀመሪያ ስም የማግኘት መብታቸው የሚከበረው በተወለዱበት ተቋም ለመጀመሪያ ጊዜ በተመዘገቡበት ስም መሆኑ እየታወቀ በቅጹ ያለመመዝገባቸው ተገቢ አይደለም ብለዋል፡፡

ሆስፒታሉ ወላጆች ልጆቻቸውን በቅጹ በመመዝገብ የልደት ምስክር ወረቀት የሚያገኙበትን ሁኔታ ሊያመቻች ይገባዋል ሲሉም ጠይቀዋል፡፡

የአንኮበር ወረዳ የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መኮንን ሙሉጌታ በበኩላቸው በሆስፒታሉ ባለፉት ስድስት ወራት የወሊድ አገልግሎት ያገኙ አንዳንድ ሕጻናት በቅጹ ስላልተመዘገቡ የልደት ምስከር ወረቀት ለመስጠት መቸገራቸውን ተናግረዋል፡፡

የደብረ ብርሃን ሪፈራል ሆስፒታል የማዋለጃ ክፍል አስተባባሪ አቶ ወንደወሰን ዳኜ በሆስፒታሉ በግማሽ ዓመቱ ውስጥ 1ሺህ 761 እናቶች መውለዳቸውን አስታውቀዋል፡፡

ሆስፒታሉ ባለበት የባለሙያዎች እጥረትና በሥራ ጫና ሳቢያ በቅጹ ያልመዘገባቸውን ሕጻናትን  መረጃ ከባህር መዝገብ በማጣራት መስጠቱን ገልጸዋል፡፡

በአማራ ክልል የሰሜን ሸዋ ዞን አስተዳደር ጽህፈት ቤት የወሳኝ ኩነቶች መረጃ ምዝገባ ቅበላ ትንተናና ጥራት ቁጥጥር ቡድን መሪ አቶ ኤልያስ እምየው በጤና ተቋማት አመራሮችና ባለሙያዎች ግድየለሽነት የወሳኝ ኩነት ምዝገባ በአግባቡ እንደማይከናወን ይናገራሉ፡፡

በደብረ ብርሃን ሪፈራል ሆስፒታል በግማሽ ዓመቱ ውስጥ ከተወለዱት   ሕፃናት 31ዱ በቅጡ እንዳልተመዘገቡ አስረድተው፤ ሆስፒታሉ ችግሩን እንዲፈታም  በደብዳቤ ማሳወቃቸውን ገልጸዋል።

ቅጹ ከተሞላ በኋላ የሚሰጠው የልደት ምስክር ወረቀት ማህበራዊ፣ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጥቅም እንዳለውም በመጠቆም።

የሰሜን ሸዋ ዞን ጤና መምሪያ የእቅድና ክትትል ባለሙያ አቶ ወንድም አገኘሁ ገብረመላክ በበኩላቸው ቀደም ሲል ወረዳን መሠረት ያደረገ የመረጃ ሥርዓት ቢዘረጋም፤ ሥርዓቱ የወሳኝ ኩነት ምዝገባን ቅጽን ባለማካተቱ ክፍተቱ መፈጠሩን አስረድተዋል።

በዚህም ምክንያት ባለፉት ወራት በአንዳንድ ጤና ተቋማት ምዝገባ ያለመካሄዱን አመልክተዋል።

አሁን ግን ምዝገባው በሥርዓቱ ተካቶ ሥራ በመጀመሩ ችግሩን  እንደሚፈታ እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡

በአትዮጵያ የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ በአዲስ መልክ ሥራ ላይ መዋል የጀመረው ከ2008 ጀምሮ ነው።