በቻይና በሚካሄደው አለም አቀፍ የቴክኖሎጂ ውድድር ሁለት ኢትዮጵያውያን ይሳተፋሉ

1023

አዲስ አበባ  የካቲት 26/2011 በቻይና በሚካሄደውአለም አቀፍ የቴክኖሎጂ ውድድር ሁለት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ኢትዮጵያን ወክለው ይሳተፋሉ።

‘ሁዋዌ’ የተሰኘው ተንቀሳቃሽ ስልክ አምራች በኢትዮጵያ ያዘጋጀውና ለሶስት ወራት የቆየው የቴክኖሎጅ  ውድድር  ከፍተኛ ዉጤት ላመጡ  ስድስት ተማሪዎችና አንድ መምህር እዉቅናና ሽልማት ተሰጥቷል።

ከአሸናፊዎቹ መካከል ሁለቱ ተማሪዎች ኢትዮጵያን ወክለዉ በዓለም ዓቀፍ የመገናኛ ኢፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዉድድር እንደሚሳተፉም ተጠቅሷል።

ይብራ መሀሪ እና ያሬድ ረዳ የተባሉ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ኢትዮጵያን ወክለዉ  ቻይና በሚደረገዉ አለም ዓቀፋዊ የመገናኛ ኢፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዉድድር እንደሚሳተፉ ታውቋል።

ህዋዌ ለሶስት ወራት በኢትዮጵያ ያካሄደው የቴክኖሎጂ ዉድድር የፍጻሜ ስነ-ስርዓት ዛሬ ሲካሄድ የህዋዊ በኢትዮጵያ ዳይሬክተር ቴድ ሜንግዩ እንደገለጹት፤ ውድድሩ ለዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የቴክኖሎጂ ሽግግር ለማድረግ፣ የትምህርት አቅምን ለማዳበርና ዓለም ዓቀፍ ተወዳዳሪነትን ያሳድጋል።

በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የምርምርና የኔትወርክ ዳይሬክተር አቶ ዘላለም  አሰፋ  በአገሪቱ ያለዉ የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ  እንዲያድግ ለማድረግ ተማሪዎች ዓለም ዓቀፍ ዕውቅና ካለው ተቋም ጋር እንዲሰሩ የሚደረግ መሆኑን ገልጸዋል።

የቴክኖሎጂ ዘርፍ ተማሪዎች ትምህርታቸውን አጠናቀው ሲወጡ የአገሪቱን የቴክኖሎጂ ችግር ለመፍታት የሚያስችል አቅም ይዘው እንዲወጡና ዓለም ዓቀፍ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ከተለያዩ አካላት ጋር ትስስር መፍጠር እንደሚጠበቅባቸው ጠቁመዋል።

ተማሪዎች አዳዲስ የፈጠራ ስራዎችን ሰርተዉ በአለም አቀፍ ደረጃ ራሳቸዉን የማስተዋወቅ ችግር እንዳለባቸው የገለጹት አቶ ዘላለም ተማሪዎቹ የሚያመነጯቸውን የቴክኖሎጂ ፈጠራዎች ማስተዋወቅ እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።

በዉድድሩ ለሽልማት የበቁት የመቐለ ዩኒቨርሲቲ መምህር አቶ የማነ ሰገደ የሚሰሩበት ዩኒቨርሲቲ ለማስተማሪያ የሚሆኑ ቁሳቁሶችን በተገቢዉ መንገድ በማቅረብና ተገቢውን እገዛ ስላደረገላቸው አሸናፊ ለመሆን እንደበቁ ተናግረዋል።

ተማሪዎችን ተግባር ተኮር የሆነ ትምህርት በማስተማር አለም ዓቀፍ ተወዳዳሪ እንዲሆኑና አገር በቀል የሆኑ ድርጅቶች እንዲኖሩ መሰራት እንዳለበትም ጠቁመዋል።

በውድድሩ አሸናፊ የሆነው የመቐለ ዩኒቨርስቲ ተማሪ ይብራ መሀሪ መምህራን ከሚያደርጉለት ድጋፍ በተጨማሪ በግሉ ብዙ መረጃዎችን በማንበብ እና ከጓደኞቹ በማግኘት ለስኬት ሊበቃ እንደቻለ ገልጿል።

በወድድሩ 20 የትምህትርት ተቋማትና ከ4 ሺህ በላይ የሚሆኑ ተማሪዎች ተሳትፈዋል።

ህዋዊ በአለም አቀፍ  የመገናኛና ኢፎርሜሽን ቴክኖሎጅ እዉቅና ያለዉ ሲሆን በ140 አገሮች አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።