የኢትዮጵያን ቱሪዝም ተወዳዳሪነት ለማሻሻል የሚያስችል የትብብር ስምምነት ተፈረመ

660

አዲስ አበባ  የካቲት 26/2011የኢትዮጵያን ቱሪዝም ዘርፍ ተወዳዳሪነት የሚያሳድግ የትብብር ስምምነት በቱሪዝም ኢትዮጵያ እና በለም አቀፉ የፋይናንስ ትብብር /አይ ኤፍ ሲ/ መካከል ተፈረመ።

ስምምነቱን የተፈራረሙት የአለም አቀፉ የፋይናንስ ትብብር የምስራቅ አፍሪካ ዳይሬክተር ጁሙኬ ጃጋን ዱኩናሙ እና የቱሪዝም ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ወይዘሮ ሌንሳ መኮንን ናቸው።

አሁን የተፈረመው ስምምነት ዘርፉ ለአገራዊው ምጣኔ ኃብት አድገት የበኩሉን ሚና እንዲጫወት የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ የሚያስችል ነው ተብሏል።

ዓለም አቀፉ የፋይናንስ ትብብር  ዳይሬክተር ጁሙኬ ጃጋን ዱኩናሙ ኢትዮጵያ በቱሪዝም ዘርፍ መልካም እድሎች ያላት አገር በመሆኑ ይህንን መደገፍ አስፈላጊ ነው ብለዋል።

ዳይሬክተሩ እንደገለጹት ፤ “የቱሪዝም ሴክተሩ በዓለም ከፍተኛ የሰው ኃይል ቀጣሪ ከሆኑ አገልግሎቶች  አንዱ ነው”

የዓለም ባንክ ክንፍ ከሆነው ይኸው ተቋም ጋር የተደረሰው ስምምነት ለኢትዮጵያ ቱሪዝም ዘርፍ የአቅም ግንባታ ድጋፍ በማድረግ ዘርፉ ለምጣኔ ኃብት እንቅስቃሴው የሚጫወተውን ሚና ለማሻሻል እንደሚረዳ ታምኖበታል።

ለመጪዎቹ ሶሰት ዓመታት የሚቆየው የስምምነቱ ማዕቀፉ ለቱሪዝም ኢትዮጵያና ለሌሎች የመንግስት እና የግል ተቋማት የአቅም ግንባታ ድጋፍና ዓለም ዓቀፍ የፋይናንስ ትብብር ያመቻቻል።

በትብብር ስምምነቱ በመታገዝ የኢትዮጵያ የቱሪዝም ኢንዱስትሪ የሚመራበት ዘመናዊና አዲስ የቱሪዝም ገበያ መሳቢያ መንገዶች ይዘጋጃሉ። 

አዲስ አበባ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ መቀመጫ ከመሆኗ ጋር ተያይዞ የኮንፍረንስ ቱሪዝም ማዕከል እየሆነች መምጣቷ፣ በዓመት 10 ሚሊዮን የሚደርሱ መንገደኞች የኢትዮጵያ አየር መንገድን መጠቀማቸው እንዲሁም የነፃ ቪዛ አገልግሎትን መጀመር ሴክተሩ ያለውን ጠቀሜታ እንደሚያሳይ አንስተዋል።

የቱሪዝም ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ወይዘሮ ሌንሳ መኮንን በበኩላቸው፤ከዓለም አቀፉ የፋይናንስ ትብብር ጋር የተደረገው የድጋፍ ስምምነት በኢትዮጵያ ዘመናዊው የቱሪዝም ኢንዱስትሪ የሚመራበት አዲስ የቱሪዝም ገበያ መሳቢያ መንገዶችን ለመጠቀም እንደሚረዳ አስረድተዋል።

ስምምነቱ የመንግስትና ግል ተቋማት ለዘርፉ እድገት በቅንጅት ለመስራትና የመረጃ ማጠናከርና ማደራጀት ሥራን ለማዘመን ይረዳል።

ትበብሩ ከዚህ ባለፈ አዲስ አበባን ይበልጥ የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ የሚያስችል ሥራ ለማከናወን የሚጠቅም የአቅም ግንባታ ድጋፍ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ ባለፈው የፈረንጆች ዓመት ሁለተኛው ግማሽ ዓመት ከቱሪዝም ያገኘችው ጠቅላላ ገቢ 1 ነጥብ 4 የአሜሪካ ዶላር ሲሆን ይህም የእቅዱ ግማሽ ያህል ብቻ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ።

አገሪቱ በተጠቀሰው ወቅት ከዘርፉ ለመሰብሰበ አቅዳ የነበረው 2 ነጥበ 7 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ነው።