በክልሉ የተፈጥሮ ሀብት ልማት ሥራው ከግማሽ በላይ መከናወኑ ተጠቆመ

732

መቀሌ የካቲት 25/2011 በትግራይ ክልል የተፈጥሮ ሀብት ልማት ሥራ ለማከናወን ዘንድሮ በዕቅድ ከተያዘው ከ50 በመቶ በላይ ለማከናወን መቻሉን የክልሉ ግብርናና ገጠር ልማት ቢሮ አስታወቀ።

በቢሮው የህዝብ ግኑኝነት ኃላፊ አቶ ሚኪኤለ ምሩጽ ለኢዜአ እንዳሉት የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራው ካለፈው የካቲት 1 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ እየተካሄደ ያለው በአርሶ አደሮች ነጻ ጉልበት አስተዋጽኦ ነው።

በእዚህም ዘንድሮ 1 ሺህ 406 ተፋሰሶችን የሚሸፍን የእርከን ሥራ ለማከናወን ታቅዶ ወደሥራ መገባቱንና ይህም 70 ሺህ ሄክታር መሬትን ከጎርፍ አደጋ ነጻ ያደርጋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።

አቶ ሚኪኤለ እንዳሉት ዘንድሮ ለማከናወን ከታቀደው የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ ውስጥ እስካሁን ድረስ 50 በመቶ የሚሆን ሥራ ተጠናቋል።

ቀሪውን 50 ከመቶ የሚሆነውን ሥራ እስከ መጋቢት አጋማሽ ወር ድረስ ለማጠናቀቅ በትኩረት እንደሚሰራም አመልክተዋል።

በልማት ሥራው ከ1 ሚሊዮን የሚበልጥ የክልሉ ህዝብ ነጻ የጉልበት አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑን የገለጹት ኃላፊው፣ በቀጣይም አካባቢውን ከሰው ሰራሽና ከተፈጥሮ አደጋ ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ድጋፉን እንዲያጠናክር ጠይቀዋል።

በትግራይ ደቡባዊ ዞን እምባአላጀ ወረዳ የአመድ ውሃ ገጠር ቀበሌ አርሶ አደር አብረሃ ሐገዞም በአካባቢያቸው በሚገኝ ተራራማ ስፍራ ላይ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ በማከናወን ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በተነሳሽነት በዘመቻ እያከናወኑ ያለው የልማት ሥራ በእርሻ መሬት ላይ ሲደርስ የነበረውን የጎርፍ አደጋ ለማስቀረት ጠቀሜታ እንዳለው ተናግረዋል።

ከእዚህ በተጨማሪ ከተፋሰሱ በታች ለመስኖ ልማት የሚያገለግሉ ምንጮች በቅርብ ርቀት እንዲገኙና እንዲጎለብቱ ማድረጉን በተጨባጭ ማረጋገጣቸውን ገልጸዋል።

ባለፉት ዓመታት ባከናወኗቸው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎች ከዚህ ቀደም ደረቅ በሆኑ አካባቢዎች ጭምር ውሃ በትንሽ ሜትር ርቀት ላይ ቆፍሮ ለማግኘት እንዳስቻላቸው የገለጹት ደግሞ ወይዘሮ ሙሉ አማረ የተባሉ ነዋሪ ናቸው።

የተገኘውን የውሃ ሃብት በመጠቀም በግማሽ ሄክታር መሬታቸው ላይ በዓመት ሁለት ጊዜ እያለሙ ተጠቃሚ መሆናቸውንና በእዚህም በየዓመቱ ልማቱን እያጠናከሩ መምጣታቸውን ተናግረዋል።

ያከናወኗቸው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎች ከራሳቸው አልፎ ለልጅ ልጆቻቸው ኢኮኖሚያዊ መሰረት ሆኖ እንዲያገለግል ተገቢውን ጥበቃና እንክብካቤ እንደሚያደርጉም አስታውቀዋል።

“ባለፉት ዓመታት በተሰሩ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎች በአካባቢያችን የሚገኙ የተራቆቱ ተራሮች ሙሉ በሙሉ አገግመዋል” ያሉት ደግሞ የወረዳው ነዋሪ አባ ገብረሰላማ ለአከማርያም ናቸው።

የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራው በትክክል ለም አፈር እንዳይሸረሸር ከመከላከል በላፈ የአካባቢን ሙቀት ለመከላከልና የመሬት እርጥበትን ጠብቆ ለማቆየት ጠቀሜታ እንዳለው በተጨባጭ ማረጋገጣቸውንም አመልክተዋል።

እሳቸው እንዳሉት የተወሰኑ የአካባቢው ወጣት አርሶ አደሮች በህዝብ ነጻ ጉልበት በለሙ ተራሮች ላይ በንብ ማነብ ሥራ ተሰማርተው ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን እየጠቀሙ ነው።