ኤጀንሲው አሰራሩን ለማዘመን የአገልግሎት ክፍያ ስርዓቱን ሊቀይር ነው

629

አዲሰ አበባ የካቲት 25/2011 የሰነዶች ምዝገባና ማረጋገጫ ኤጀንሲ አሰራሩን ለማዘመን የአገልግሎት ክፍያ ስርዓቱን ሊቀይር መሆኑን ገለጸ።

ለዚህ ያግዘው ዘንድ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር የሲቢኢ ብር አገልግሎት ስምምነት ተፈራርሟል።

ስምምነቱን የተፈረሙት የሰነዶች ምዝገባና ማረጋገጫ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር እና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የባንክ አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ናቸው።

የሰነዶች ምዝገባና ማረጋገጫ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ መረሳ ገብረህይወት እንዳሉት የአሰራር ስርዓቱን ለተገልጋይ በሚያመች መልኩ በማዘመን ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት ጥናት ተደርጓል።

በመሆኑም አገልግሎቱን ለመጀመር በሁለቱ ተቋማት መካከል ትናንት ስምምነት የተደረገ ሲሆን ደንበኞች የአገልግሎት ክፍያቸውን በሲቢኢ ብር ይፈጽማሉ።

ዋና ዳይሬክተሩ “አሰራሩ ጥሬ ገንዘብ በተቋሙ ስለማይኖር ከተለያዩ ስጋቶች ከማሳረፉ ባሻገር ደንበኞች የሚያነሱትን ቅሬታም ይፈታል” ብለዋል።

በቀደመው አሰራር ደንበኞች ከአገልግሎት በፊት ክፍያ እንዲፈጽሙ ይደረግና ከከፈሉ በኋላ በተለያየ ምክንያት “ይህን አገልግሎት ማግኘት አትችሉም” ሲባሉ ቅሬታ ያቀርቡ እንደነበር ጠቅሰው ይህን መሰሉን ቅሬታ ለመፍታት እንደሚያስችል ነው የገለጹት።

ከዚህ በተጨማሪ በክፍያ ወቅት የሚታየውን ሰልፍ እንደሚያስቀርም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የባንክ አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር አቶ ደረጄ ፉፋ በበኩላቸው ባንኩ በተቋማት ላይ የሚፈጠረውን መስተጓጎል ለማስቀረት እየሰራ መሆኑንና እንደ ኤጀንሲው ሁሉ በሌሎች ተቋማትም ለመጀመር መታሰቡን ገልጸዋል።

በኔትወርክ መቆራረጥ ምክንያት እየደረሰ ላለው ቅሬታ ከአጋር አካላት ጋር በመቀራረብ የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።