በሕዝብና ቤቶች ቆጠራ ጥቅም ላይ በሚውሉ ግብአቶች ዙሪያ ገለጻ ተደረገ

805

አዲስ አበባ የካቲት 25/2011 የማእከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲና የፌዴራል ፕላንና ልማት ኮሚሽን ዘንድሮ ለሚካሄደው የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ ጥቅም ላይ በሚውሉ ግብአቶች ዙሪያ ገለጻ አድርገዋል።

ገለጻውን ያደረጉት ከክልልና ከተማ አስተዳደር ለመጡ የኮሙኒኬሽን ቢሮ ሃላፊዎች፣ የአገር ሽማግሌዎችና ለሃይማኖት አባቶች ነው።

አራተኛው ዙር የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ ከመጋቢት 29 እስከ ሚያዚያ 20 ቀን 2011 ዓ.ም በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች ይካሄዳል።

የፕላንና ልማት ኮሚሽነር ዶክተር ፍጹም አሰፋ የህዝብና ቤት ቆጠራ ፋይዳ፣ የህዝብና ቤት ቆጠራ የትግበራና የዝግጅት ወቅት ስራዎች፣ በህዝብና ቤት ቆጠራ የባለድርሻ አካላት ሚና፣ ስታስቲካዊ መረጃዎች ያላቸው ጠቀሜታና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ  ጽሁፍ አቅርበዋል።

በጽሁፉ በቆጠራ ወቅት ሙያተኞች ስለሚጠቀሙበት ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችና ሌሎች አስፈላጊ ግብአቶችን አጠቃቀም በሚመለከት አብራርተዋል።

በዚህም ቀደም ሲል በቆጠራ ወቅት ይከሰቱ የነበሩ የቁጥርና ሌሎች ስህተቶች እንዳይደገሙ ለማስቻልም ሙያተኞች አስፈላጊውን ስልጠና የሚያገኙበት የግብአት አጠቃቀም ላይ በትኩረት እንደሚሰራ ጠቁመዋል።

በተጨማሪም በዘንድሮው የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ ወቅት ስለ ቆጠራው ዓላማና ጠቀሜታ የህብረተሰቡን ግንዛቤ ማጎልበትና እውነተኛ መረጃ ማሰባሰብ ላይ ሙያተኞች በምን መልኩ ሊሰሩ እንደሚገባ አቅጣጫ ተቀምጧል።

በዋናነትም እኩል አገልግሎት መስጠት፣ ተጠያቂነት፣ ወጪ ቆጣቢነት፣ ምስጢራዊነትና ህግ አክባሪነት ሙያተኞቹ ሊከተሉት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በዋናነት በቆጠራው ወቅት ማንኛውም ዜጋና ቤት ሳይቆጠር እንዳያልፍ ከባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ ለመስራት የሚያስችል ዝግጅቶች መደረጋቸውንም ገልጸዋል።

ከትምህርት ሚኒስቴር፣ ከጤና ተቋማት፣ ሚዲያዎችና ሌሎች ዜጎች ከሚገለገሉባቸው ማህበራትና የግል ድርጅቶች ጋር በጋራ የሚሰራ እንደሆነና ይህም እውነተኛ መረጃን ለመሰብሰብ እንደሚያግዝ በጽሁፋቸው አብራርተዋል።