የበጀት ቀመር ድልድል ኮሚሽን ሊቋቋም ነው

165

መቀሌ የካቲት 25/2011 በጥናት ላይ የተመሰረተ ፍትሃዊ የክልሎች የበጀት ቀመር ድልድልን ተፈጻሚ ለማድረግ የሚያግዝ  ኮሚሽን የሚቋቋም መሆኑን የፌዴሬሽን ምክር ቤት አስታወቀ፡፡

በመቀሌ ከተማ በተካሄደው የፌዴሬሽን ምክር ቤትና የክልሎች የጋራ ምክክር መድረክ ላይ የበጀት ድልድል ኮሚሽን  ለማቋቋም  የተዘጋጀ  ረቂቅ አዋጅ  ለውይይት ቀርቧል፡፡

በፌዴሬሽን ምክር ቤት የገቢ ክፍፍል ጥናት ከፍተኛ ባለሙያ ዶክተር ዘውዱ ከበደ በመድረኩ እንዳሉት፣ ኮሚሽኑ ያስፈለገው ለክልሎች የሚደለደለውን የበጀት ድልድል ቀመር ህግና ስርዓት የተከተለ እንዲሆን ለማስቻል ነው።

ባለፉት ዓመታት የነበረው የክልሎች የበጀት ድልድል ህግና ስርዓት የተከተለ ሳይሆን አለተጠያቂነት በመተማመንና በመተሳሰብ ላይ የተመሰረተ ሆኖ ቆይቷል፡፡

በመተሳሳብ ሲደረግ የነበረው ድልድል ተደጋጋሚ የበጀት እና የተጨማሪ የገንዘብ ድጎማ ጥያቄዎች ከተለያዩ ክልሎች ሲቀርብ እንደነበረና   ይህም  በፍትሃዊነት ላይ ችግር እንዳለበት ሲተች እንደቆየ  ገልጸዋል፡፡

ከአሁን በኋላ የሚኖር የበጀት ጥናትና ትግበራ ህግና ስርዓት የተከተለ፣ ችግር ሲኖርም ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ቀርቦ የማያዳግም ውሳኔ የሚያሰጥ ጠንካራ ኮሚሽን ማስፈለጉን አስታውቀዋል።

የበጀት ድልድል ኮሚሽን ለማቋቋም የተዘጋጀው ረቂቅ አዋጁ በመቀሌው መድረክ ለማዳበር ቢሆንም ቀደም ሲል የሁሉም የክልሎች  ምክር ቤቶች ተወያይተውበት ተቀባይነት ማግኘቱን አመልክተዋል።

እንደ ዶክተር ዘውዱ ገለጻ ፣ረቂቅ አዋጁ በቀጣይ ወራት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ እንደሚጸድቅ ይጠበቃል።

በረቂቅ አዋጁ ዝግጅት ከተሳተፉ ምሁራን መካከል አቶ ፀጋብርሃን ታደሰ  እንዳስረዱት የቀረበው ረቂቅ አዋጅ ቀደም ሲል ሲታዩ የነበሩት ድክመቶች እንዳይደገሙና  ህጋዊ መሰረት ያለው የበጀት ድጎማ ለመከተል የሚያግዝ ነው፡፡

የቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ሃብታሙ ታዬ  በሰጡት አስተያየት ኮሚሽኑን ለማቋቋም የተዘጋጀው ረቂቅ አዋጅ የሚደገፍ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በመቀሌ ከተማ ለሁለት ቀናት በተዘጋጀውና ትናንት በተጠናቀቀው  የክልሎች የበጀት ቀመርና ድጎማ  ረቂቅ አዋጅ ላይ በመከረው መድረክ  የየክልሉ  አፈ ጉባኤዎች፣ የምክር ቤቶች  ቋሚ ኮሚቴዎችና  ምሁራን ተሳትፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም