ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ የስራ ጊዜያቸውን ያጠናቀቁትን የኳታር አምባሳደር አሰናበቱ

4204

አዲስ አበባ ግንቦት 22/2010 የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ የስራ ጊዜያቸውን ያጠናቀቁትን የኳታር አምባሳደር አብዱላዚዝ ሱልጣን ጃሲም አል_ሩማሂን አሰናብተዋል።

ፕሬዝዳንቱ በጽህፈት ቤታቸው ከአምባሳደሩ ጋር በነበራቸው ቆይታ ኳታር ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማጠናከር የተደረሱ ስምምነቶችን ተፈጻሚ ማድረግ በሚቻልበት ሁኔታ መክረዋል።

በተለይም ሁለቱ አገሮች በኢንቨስትመንት መስክ ያላቸውን ግንኙነት ውጤታማ ለማድረግ አምባሳደር አብዱላዚዝ ወደአገራቸው በሚመለሱበት ጊዜ የአገሪቱ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ ስላለው ሰፊ የኢንቨስትመንት አማራጭ እንዲገነዘቡ ለማድረግ እንዲሰሩ ፕሬዝዳንቱ አስገንዝበዋል።

ውይይቱን የተከታተሉት የፕሬዚዳንቱ ጽህፈት ቤት የኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ከፍተኛ ባለሙያ አብርሃም ግርማይ እንደገለጹት፤ የኳታር ባለሃብቶች በኢትዮጵያ ኢንቨስት እንዲያደርጉ ለማስቻል አምባሳደሩ የላቀ ሚና መጫወት ይችላሉ።

አምባሳደር አብዱላዚዝ ሱልጣን ጃሲም አል_ሩማሂ በበኩላቸው የኢትዮጵያና የኳታር ግንኙነት እንዲጠናከር የሚሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ በነበራቸው የስራ ቆይታ ስኬታማ ጊዜ እንዲያሳልፉ ድጋፍ ላደረጉላቸው አካላት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።