በኢትዮጵያ ከአምስት ሚሊዮን ዜጎች በላይ ለመስማት ችግር የተጋለጡ እንደሆነ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ከአምስት ሚሊዮን ዜጎች በላይ ለመስማት ችግር የተጋለጡ እንደሆነ ተገለጸ
አዲስ አበባ የካቲት 24/2011 በኢትዮጵያ 5 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዜጎች ለመስማት ችግር የተጋለጡ እንደሆነ ተገለጸ።
''የዓለም የመስማት ቀን" በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል አዘጋጅነት ዛሬ በአዲስ አበባ ተከብሯል።
በዓለም 1 ቢሊዮን ሰዎች ለመስማት ችግር የተጋለጡ ሲሆን፤ ከነዚህ 80 በመቶ የሚሆኑት የችግሩ ተጠቂዎች ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ያላቸውና ከሰሃራ በታች የሚገኙ አገሮች እንደሆነ ተገልጿል።
ዶክተር አለነ መሻሻ በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም የህክምና ኮሌጅ የአንገት በላይ ህክምና መምህር በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፣ በአገራችን 5 ነጥብ 3 ሚሊዮን የሚሆኑት ዜጎች ለዚሁ ችግር የተጋለጡ እንደሆኑና ይህም በኢንፌክሽን ምክንያት እንደሚመጣና ችግሩም በህጻናት ላይ እንደሚበዛ ገልጸዋል።
አዲስ የተወለዱ ጨቅላ ህጻናት በእናት ማህጸን እያሉም በሚኖር ኢንፌክሽን ምክንያት፣ በክብደት ማነስ፣ የደም ማነስ ያለባቸው ህጻናት በተለይ በህጻናት ጽኑ ህሙማን በተለያየ ኢንፌክሽን ምክንያት የተኙ ህጻናት በከፍተኛ ሁኔታ ለመስማት ችግር የተጋለጡ እንደሆነ ተገልጿል።
በአዋቂዎች ላይ በስራ ቦታቸውና በመዝናኛ አካባቢዎች ላይ ለከፍተኛ የድምጽ መጠን መጋለጥ፣ በጆሮ ማዳመጫዎች፣ የመድሃቶች የጎንዮሽ ጉዳት፣ የእድሜ መግፋት፣ ከደም ግፊትና ከስኳር ህመም ጋር በየታያያዘም ችግሩ እንደሚከሰት ዶክተር አለነ አብራርተዋል።
የመስማት ችግርን በየደረጃው ታክሞ የሚድን እንዳለና ነገር ግን ከግንዛቤ ማነስ እንዲሁም በዘርፉ ያሉ የህክምና ባለሙያዎች በቁጥር ማነስ የተነሳ ችግሩ ስር እንዲሰድ ምክንያት እንደሆነ ደግሞ ዶክተር ነጋ ኪሮስ የአንገት በላይ ቀዶ ህክምና እስፔሻሊት ይናገራሉ።
ችግሩን ለመፍታትም እንደ አገር በዘርፉ በቂ ባለሙያዎችን ማፍራት እንደሚጠበቅና በህክምና ስራ ላይ ያሉትን ባለሙያዎችንም በማሰልጠን ህክምናውን ተደራሽ ማድረግ እንደሚገባ ዶክተር ነጋ አክለዋል።
ለዚሁ ችግር መፍትሔ የተዘጋጀ ፍኖተ ካርታ መኖሩንና ፍኖተ ካርታው በስራ ላይ ሲውል በየደረጃው ላሉት የህክምና ባለሙያዎች ስልጠና በመስጠትና ለህክምናው የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶችን በማሟላት በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ሊሰራበት መታቀዱም ተጠቁሟል።
ህክምናው የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታልን ጨምሮ በራስ ደስታ፣ በጥቁር አንበሳ አስፔሻላይዝድ ሆስፒታል፣ በየካቲት 12 ሆስፒታል፣ በሚኒሊክ ሆስፒታል ፣ በፖሊስ ሆስፒታልና በጦር ኃይሎች ሆስፒታል እንደሚሰጥ ተገልጿል።
ሲቢኤም የተሰኘ የጀርመን ግብረ ሰናይ ተቋም በኢትየጵያ በዘርፉ ያለውን ችግር ለመፍታት በገንዘብና በቁሳቁስ እየረዳ እንዳለም ተገልጿል።