ማይጨው ላይ አርበኞችንና ታሪካዊ ሁነቶችን የሚዘክር ሙዚየም እንዲገነባ ተጠየቀ

87

ማይጨው የካቲት 24/2011በ1928 ዓ.ም የጣልያን ወረራ በማይጨው በደረሰው የጣልያን/ፋሺስት የመርዝ ጋዝ ጭፍጨፋ የተሰው ከ30 ሺህ በላይ አርበኞችና ሌሎች ታሪካዊ ሁነቶችን የሚዘክር ደረጃውን የጠበቀ ሙዚየም እንዲገነባ ተጠየቀ።

የትግራይ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ በበኩሉ ታሪካዊ ሁነቶችን የሚዘክር ሙዚየም ለመገንባት ስራ መጀመሩን አስታውቋል።

በትግራይ ክልል ደቡባዊ ዞን የምትገኘው ማይጨው ከ1888ቱ የአድዋ እንዲሁም ከ1928 ዓመተ ምህረቱ የማይጨው ጦርነቶች ጋር የተሳሰረች ታሪካዊ ስፍራ ናት።

ከታሪካዊ ሁነቶች መካከል ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ወደ አድዋ ሲዘምቱ ያረፉባት፣ የሰራዊታቸው የጭነት ፈረሶቻቸውና በቅሎዎቻቸው ላይ በሽታ ማጋጠሙን ተከትሎ ፀበል ያገኙበትና የተፈወሱበት የማይጨው ደብረ ጽጌ አቡነ ተክለሃይማኖት ገዳም ይገኛል።

የዚህ ገዳም አገልጋይ መምህር ከበደ ባራኪ ለኢዜአ እንደገለጹት ቤተክርስቲያኗ በ17ኛው ክፍለ ዘመን በአፄ ኢያሱ ተመስርታ በዳግማዊ አፄ ምኒልክ የተገደመችና በርካታ ታሪካዊ ቅርሶችን የያዘች ጥናታዊት ገዳም ነች።

በገዳሙ ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ያበረከቱት ከ30 በላይ የብራና መጻህፍት፣ የአፄ ምኒልክ ፎቶግራፍና አልባሳት፣ ንዋየ ቅድሳት፣ የተለያዩ ነገሥታት ደብዳቤዎችና ሌሎችም ቅርሶች እንደሚገኙ ለአብነት ጠቅሰዋል።

ታሪካዊቷ ስፍራ ንጉሠ ነገሥቱ ወደ ጦርነቱ ሲሄዱና ሲመለሱም ያረፉባትና ለድሉ የመንፈስ ስንቅ የሆነች ብትሆንም የአድዋ ድል ሲዘከር ግን ስሟ እንደማይነሳ ይገልጻሉ።

ገዳሟ ሙዚየም ለመገንባት አቅም እንደሌላትም አክለዋል።

በሌላ በኩል በ1928 ዓ.ም በአድዋ ድል የተመታው ጣልያን/ፋሺስት ዳግም ኢትዮጵያን በወረረበት ወቅት በአውሮፕላን በተርከፈከፈ መርዝ ያለቁ ከ30 ሺህ በላይ አርበኞች አጽም ያረፈበት የማይጨው መካነ-ሠማዕታት ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያንም ይገኛል።

ከአምስት ዓመት ወረራ በኋላ የሠማዕታቱ አጽም ተሰብስቦ በአፄ ሃይለ ስላሴ የመታሰቢያ ሀውልት ቢቆምላቸውም በደርግ ጊዜ አጽሙ በስፍራው ወደሚገኝ የጦር ካምፕ ተዘዋውሮ እንደነበር የትግራይ ደቡባዊ ዞን ቤተ ክህነት ፀሐፊ ሊቀ ትጉሃን ረዳኢ ብርሃኑ ተናግረዋል።

ቤተክርስቲያኗ ከደርግ ውድቀት በኋላ የአርበኞቹን አጽም ከጦር ካምፑ አስነስታ በአነስተኛ ሙዚየም በክብር አስቀምጣለችም ብለዋል።

በጦርነቱ ከሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢ የተውጣጡ አርበኞች የተሳተፉበትና የጋራ ታሪክ መሆኑን ገልጸው ይሁንና 'ሙዚየሙ በአግባቡ አልተዋወቀም አልተዘከረምም' ነው ያሉት።

የትግራይ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ቢሮ ሀላፊ ወይዘሮ ዘነቡ ሀፍቶም ማይጨው በርካታ የጦርነት ታሪኮችን ያስተናገደችና በዙሪያዋ ታሪካዊና ተፈጥሯዊ ስፍራዎችን ያቀፈች ብትሆንም ብዙም ትኩረት ሳይሰጣት መቆየቷን ጠቁመዋል።

ማይጨው ከአድዋ ጦርነት ጋር ከመተሳሰሯ በተጨማሪ በ1928 ዓ.ም ወረራ ከባድ መስዋዕትነት የተከፈለባት ስፍራ በመሆኗ የሰማዕታትን ጨምሮ ታሪካዊ ሂደቱን የሚገልጽ ሙዚየም ለመገንባት መታቀዱን ገልጸዋል።

ለሙዚየም ግንባታ የሚውል ቦታ መለየቱን ገልጸው በቀጣይ የበጀት ማሰባሰብ ስራው ይከናወናል ብለዋል።

በማይጨው የ1928 ዓመተ ምህረቱ ጦርነት ስፍራ የንጉሱ ማረፊያ ዋሻ፣ አሸንጌ ሐይቅ እንዲሁም በቅርብ ርቀት የአምባላጌ የጦርነት ታሪካዊ ስፍራዎች ይገኛሉ።

ክልሉ ታሪካዊ ፍስራዎችን የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ እንደሚሰራ ምክትል ቢሮ ሃላፊዋ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም