በሸማቾች ላይ የሚደርሰውን የዋጋ ጫና ለመቀነስ የትርፍ ጣሪያ ሊቀመጥ ይገባል-ጥናት

59

አዲስ አበባ  የካቲት 24/2011 በኢትዮጵያ ያለው የነፃ ገበያ ምጣኔ ሀብት ስርዓት በምርቶች ዋጋ ላይ የትርፍ ህዳግ ወሰን ባለማስቀመጡ በሸማቾች ላይ ጫና እያሳደረ መሆኑን የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ጥናት አመለከተ።

ትክክለኛ የሚዛን ልኬት በገበያ ውስጥ አለመኖርም በኅብረተሰቡ ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ማባባሱ ተጠቁሟል።

ጥናቱ አራት የህግና አስር የአሰራር ክፍተቶችን የለየ ሲሆን፤ የንግድ አሰራርና ሸማቾች ጥበቃ አዋጅን በተደጋጋሚ ማሻሻል፣ የአመለካከትና የግንዛቤ እጥረት ችግር፣ የፍላጎትና አቅርቦት አለመጣጣም፣ የህግ የበላይነትን አለማስከበር፣ የኪራይ ሰብሳቢነት፣ ተጠያቂነት አለመኖር፣ የክትትልና ቁጥጥር ማነስ፣ የንግድ ስርዓቱ በፍትሃዊ ውድድር ላይ አለመመስረት እንዲሁም የገበያ ዋጋ አለመረጋጋትና የሸማቾች መብታቸውን የማስጠበቅ አቅም አነስተኛ መሆን ጥናቱ የለያቸው ችግሮች ናቸው። 

የነፃ ገበያ ምጣኔ ሀብት ስርዓቱ የተመረጠና የተቀናጀ የመንግስት ጣልቃ ገብነትን የሚፈቅድ ቢሆንም የንግዱ ማኅበረሰብ የምርቶችን ዋጋ እስከ መቶ እጥፍ እንዲሆን ማድረጉንም ጥናቱ አረጋግጧል። 

በገበያ ዋጋ ላይ አመለረጋጋት ከሚፈጥሩ ሰው ሰራሽ ጉዳዮች ውስጥ የምርቶች የተዛባ ክምችት ሲሆን የንግዱ ማኀበረሰብ ወደፊት ያለው የገበያ ዋጋ ግምት በማስቀመጥና አላስፈላጊ የገበያ ውጥረት እንዲከሰት በማድረግ የዋጋ ጭማሪ እንዲፈጠር እንደሚያደርግም ጥናቱ ጠቁሟል።

የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም የቁጥጥርና ጥናት ዳይሬክተር አቶ አዳነ በላይ እንዳሉት፤ መንግስት በአመራረት ሂደት ላይ ያሉ ወጪዎችን መሠረት በማድረግ ለገበያ የሚቀርቡ ምርቶችን አማካይ የትርፍ ህዳግ ወሰን ሊያስቀምጥ ይገባል።

የነፃ ገበያ ስርዓቱ የምርት ዋጋ በገበያ እንዲወሰን የሚያደረግ ሆኖ የትርፍ ህዳግ ገደብ ያልተቀመጠለት በመሆኑ አላስፈላጊ የገበያ ውጥረት በማስከተል በሸማቹ ላይ ጫና እያሳደረ መሆኑን በጥናቱ መረጋገጡን አስረድተዋል።

በመሆኑንም የንግዱ ማህበረሰብ ሸቀጥና አገልግሎት አቅርበው የሚያገኙት ትርፍ ጣሪያ ሊቀመጥለት እንደሚገባ አመልክተዋል።

እንደ አቶ አዳነ ገለጻ ጥናቱ በምርቶች ላይ ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ መናር መነሻ ከሆኑትና ከተለዩት አስር ጉዳዮች በተለይ የንግድ አሰራርና ሸማቾች ጥበቃ አዋጅ በስምንት ዓመት ውስጥ ሦስት ጊዜ እንዲሻሻል መደረጉ የህግ ክፍተት እንዲፈጠር ማድረጉን ጠቁመዋል።

የአዋጁን መሻሻል ተከትሎ የማስፈጸሚያ ደንብና መመሪያ ባለመውጣቱ ህጉን ተግባራዊ ለማድረግ ተፅዕኖ የፈጠረ መሆኑም በጥናቱ መረጋገጡን ገልጸዋል።     

ሌላው ትክክለኛ የሆነ የሚዛን ልኬት በገበያ ውስጥ አለመኖር ኅብረተሰቡን እየገጠመው ያለው ችግር መሆኑን የገለጹት አቶ አዳነ፤ የሚደረገው ቁጥጥርም ከሰው ኃይልና ከቴክኖሎጂ ጋር በተያያዘ የላላ እንደሆነም በጥናቱ መመላከቱን ተናግረዋል።

በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የንግድ ሥራ አመራር ማዕከል ዳይሬክተር ዶክተር ይበልጣል አሰፋ በበኩላቸው በምርቶች ዋጋ መጨመር የተነሳ በኀብረተሰቡ ላይ የሚደርሰውን ጫና ለመቀነስ ሳይንሳዊ ጥናት በማካሄድ ችግሩን ለመፍታት እንደሚሰራ ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ አምራቾችንና ሸማቾችን የሚያስተሳስር የገበያ ስርዓት እንደሌለ የገለጹት ዶክተር ይበልጣል፤ ዋጋ አንድ ጊዜ ከጨመረ የማይቀንስበት ሁኔታ እንዳለም ገልጸዋል።

በተጨማሪም የዋጋ መናር ከምርት አቅርቦትና ፍላጎት ጋር የተያያዘ በመሆኑ ምርታማነት ዝቅተኛ በሚሆንበት ወቅት በዋጋ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እንዳለውም ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ የግብርና ምርት ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ አለመስፋፋት ለገበያ ዋጋ መናር ምክንያት በመሆኑ ዘርፉን በማጠናከር የምርት አቅርቦትን ማሳደግ ተገቢ በመሆኑ ትኩረት መሰጠት እንዳለበት አመላክተዋል ጥናቱ።

በንግድ ውድድርና ሸማቾች መብት ጥበቃ ባለስልጣን የጥናትና ምርምር ዳይሬክተር አቶ መንግስቱ ሞላ እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ ያለው የገበያ ስርዓት በአቅርቦትና በፍላጎት ላይ የተመሰረተ አለመሆንና የህግ ማዕቀፍ ግልጽነት ችግር የገበያ ዋጋ ንረት እንዲፈጠር አድርጓል።

የንግድ ስርዓቱ ረጅም ሰንሰለት ያለውና ሸማቹ ኀብረተሰብ እየተጎዳ በመሆኑ የዓለም አቀፍ ተሞክሮን መሠረት በማድረግ በተመረጡ ምርቶች ላይ የትርፍ ህዳግ መጣል እንደሚገባ አስረድተዋል። 

የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ዶክተር ተሾመ አዱኛ በበኩላቸው በኢትዮጵያ ያለው የገበያ ስርዓት ብዙ ሸማች እና ጥቂት አቅራቢ ያለበት እንዲሁም የግብይት መረጃ ስርዓቱ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ያልተደገፈ መሆኑ ለዋጋ መናር ምክንያት እንደሆነ ገልጸዋል።

የሸማቾችን የመግዛትና የመጠቀም መብት ለማስጠበቅና ሰው ሰራሽ የዋጋ ንረትን ለመከላከል በሳይንሱ መሰረት የትርፍ ህዳግ ወሰን በምርቶች ዋጋ ላይ መጣል እንዳለበትም መክረዋል።

በገበያ ዋጋ መናር ምክንያት የሚጎዱ የኀብረተሰብ ክፍሎችን መጠበቅ አንዱ የመንግስት ኃላፊነት እንደሆነ የጠቆሙት ዶክተር ተሾመ፤ ሰው ሰራሽ በሆነ ምክንያት የሚፈጠር የዋጋ ጭማሪን መቆጣጣር ያስፈልጋል ብለዋል።

የነፃ ገበያ ስርዓት መርሆ ፍትሃዊ የሆነ የትርፍ መጠን እንዲኖር የሚያደርግ ሲሆን በኢትዮጵያ ውስጥ ግን ስርዓቱን በተሳሳተ መንገድ መረዳት እንዳለም ገልጸዋል።

ከረጅም ጊዜ ጀምሮ በኢትዮጵያ ውስጥ በትራንስፖርትና በነዳጅ ላይ መንግስት የትርፍ ህዳግ ወሰን ያስቀመጠ መሆኑን ያስታወሱት ዶክተር ተሾመ፤ በገበያ ዋጋ መናር ምክንያት የሚጎዱ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ለመታደግ በምርቶች ላይ የትርፍ ህዳግ ወሰን እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም