ምሁራን አገር በቀል እውቀቶች ተጠብቀው ለትውልድ እንዲተላለፉ የማድረግ ሚናቸውን አልተወጡም ተባለ

90

አዲስ አበባ የካቲት 23/2011 በኢትዮጵያ አገር በቀል እውቀቶች ተጠብቀውና ዳብረው ለትውልዱ እየተላለፉ ጥቅም ላይ እንዲውሉ በማድረግ ረገድ ምሁራን በሚፈለገው ደረጃ ሚናቸውን እየተወጡ እንዳልሆነ አንድ ጥናት አመለከተ።

የአፍሪካ ጥናትና ምርምር ባለሙያዎች ማህበር ዛሬ የተከበረውን የዓድዋ ድል በዓልን ምክንያት በማድረግ ባዘጋጀው መድረክ ላይ የቀረበ ጥናት ነው ይህን ያመለከተው።

በዚሁ ወቅት በህዝብ ለህዝብ ትስስር፣ የኪነ-ጥበብ ዘርፍን ለአገር በቀል እውቀት መጠቀምና በባህላዊ የአኗኗርና በግጭት አፈታት ስልቶች ላይ ቀደም ሲል በማህበሩ አባላት የተሰሩ ጥናቶች ለውይይት ቀርበዋል። 

የጥናት ፅሁፎቹን ያቀረቡት የማህበሩ አባልና አንቶሮፖሎጂስት ዶክተር ጌታቸው ካሳ ናቸው። 

በቀኝ ግዛት ስር ወድቀው የነበሩ የተለያዩ የአፍሪካ አገራት አገር በቀል እውቀቶቻቸውን በሚፈለገው ደረጃ ለትውልድ በማስተላለፍ ረገድ ጫና ውስጥ ገብተው እንደነበር ጥናቶቹ አመላክተዋል።

ይሁን አንጂ ኢትዮጵያ የዓድዋ ድል ባለቤትና በቀኝ ግዛት ያላለፈች አገር ብትሆንም እንደሌሎቹ የአፍሪካ አገራት ባደጉት አገራት እውቀት የታጠረ ትውልድ በስፋት እየተስተዋለባት መሆኑም ተገልጿል።

ይህም ትውልዱ በዋናነት የራሱን ዕውቀት በመያዝና ከሌሎች ደግሞ የተሻለውን በመውሰድ ሳይንሳዊ ዕውቀትን በማዳበር ተግባር ላይ ትኩረት ከማድረግ ይልቅ የሌሎች ዓለም አገራትን ባህልና የአኗኗር ዘይቤ በመከተል መጠመዱንም ጥናቱ አትቷል።

በተለይ ወጣቱ የህብረተሰብ ክፍል የሌሎች ምእራባዊያን አገራትን ባህልና ኑሮ ናፋቂ ሆኖ ማንነቱን እየዘነጋ መምጣቱን ጥናቱ አመልክቷል።

ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ በተለያዩ ዘርፍ ያሉ ምሁራን የአገር በቀል እውቀቶች ላይ እሴትን ጨምሮ ምርምር በማድረግና የተሻሉ ልምዶችን ለትውልድ በማስተላለፍ ረገድ የሚጠበቅባቸውን ሚና በአግባቡ መወጣት አለመቻላቸው እንደሆነ ነው በጥናቱ የተብራራው። 

በጥናቱ መሰረት ኢትዮጵያ የራሷ የሆነ የግጭት አፈታት ዘዴ፣ አብሮ የመኖር ባህል እንደዚሁም  ማህበራዊ ፋይዳዎች ያሉት ባህላዊና ኪነ-ጥበባዊ ስርአት ባለቤት ብትሆንም ይሄንን ስርአት የሚከተልና ለትውልድ ለማስተላለፍ ጥረት የሚያደርግ የማህበረሰብ ክፍል ጥቂት ነው።

ይህም በአሁኑ ወቅት በህዝቦች መካከል ለሚስተዋለው መከፋፈል፣ ግጭትና አለመግባባት ምክኒያት ሆኗል ነው የተባለው።

ይህንን ክፍተት ለመሙላት ከታች ጀምሮ እስከ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ድረስ ባለው የትምህርት ሂደት ውስጥ አገር በቀል እውቀት መሰረት ሊኖረው አንደሚገባ ጥናት እቅራቢው ዶክተር ጌታቸው ካሳ አሳስበዋል። 

ዕውቀትን በመጠበቅ፣ በማጎልበትና ለትውልድ በማስተላለፍ ጥቅም ላይ የሚውልበትን መላ ለመዘየድ የሚያስችል ስርአተ-ትምህርት መቅረጽ እንደሚገባም አመልክተዋል።

እየጠፋ ያለውን የመረዳዳትና መተሳሰብ የእርስ በእርስ ግንኙነት ማጠናከር ላይም እንዲሁ ምሁራኑ በስፋት ሊሰሩ እንደሚገባም አክለዋል። 

የማህበሩ ሊቀመንበር አቶ ወርቁ በላቸው በበኩላቸው እንዳሉት በዓድዋ የተገኘውን ነጻነት አዲሱ ትውልድ ጠብቆ እንዲያቆየውና የተሻለች ኢትዮጵያን እንዲገነባ ለማስቻል በአገር በቀል እውቀቶች የበለጸገ ትውልድ ማነጽ ያስፈልጋል።

ለዚህም ደግሞ የተለያዩ የጥናትና ምርምር ውጤቶችን በማከናወንና ተግባራዊ በማድረግ ረገድ ማህበሩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ለመስራት ቁርጠኛ ነው ብለዋል።

በተጨማሪም ማህበራቸው ከትምህርት ተቋማት፣ በተለያዩ ዘርፎች ከሚሰሩና ወጣቱን ተሳታፊ ከሚያደርጉ ማህበራት ጋር በጥምረት ለመስራት ዝግጁ መሆኑን ጠቁመዋል።

አገር በቀል እውቀቶችን ጠብቆ ለትውልዱ ለማስተላለፍና ከሌሎች አገራት የሚገኙ የተሻሉ ልምዶችን በመካፈል ኢትዮጵያን ለማዘመን ማህበሩ የድርሻውን እየተወጣ መሆኑን ነው አቶ ወርቁ የተናገሩት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም