ባህር ዳር 14ኛውን የአፍሪካ ቢስክሌት ሻምፒዮና ለማስተናገድ ዝግጅቷን አጠናቃለች

461

ባህር ዳር የካቲት 23/2011ባህር ዳር ለመጀመሪያ ጊዜ ለምታስተናግደው 14ኛው የአፍሪካ ቢስክሌት ሻምፒዮና ዝግጅቷን አጠናቃለች።

የኢትዮጵያ ቢስክሌት ፌዴሬሽንና ከአማራ ስፖርት ኮሚሽን ጋር በመሆን በባህርዳር መግለጫ ሰጥቷል።

የፌዴሬሽኑ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ወርቁ ገዳ እንዳስታወቁት ሻምፒዮናውን በከተማዋ ከመጋቢት 5 እስከ 10/2011 ለማስተናገድ ዝግጅቱ ተጠናቋል።

በሻምፒዮናው አዘጋጇን ኢትዮጵያን ጨምሮ 35 አገሮች እንደሚሳተፉም ተናግረዋል።

በሻምፒዮናው በወጣቶች፣ በአዋቂዎች፣ በሴቶችና በወንዶች፣ እንዲሁም በግልና በቡድን ውድድሮች ይካሄዳሉ።

ባህር ዳር ሻምፒዮናውን ለማስተናገድ የተመረጠችው ከሐዋሳ፣ ከድሬዳዋና ከመቀሌ ጋር ተወዳድራ መስፈርቶችን በማሟላቷ ነው  ብለዋል፡፡

በሻምፒዮናው ከ400 በላይ ተወዳዳሪዎች ይሳተፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ጠቁመው፤ ለተሳታፊዎች ትራንስፖርትና ሆቴሎች መዘጋጀታቸውን አቶ ወርቁ አስረድተዋል፡፡

ከሻምፒዮናው አገሪቱና ክልሉ የሚተዋወቁበትና መልካም ገፅታ የሚገነባበት መድረክ ይሆናል ብለዋል።

ኢትዮጵያ በተጨማሪ 40 የሚሆኑና የተሻለ ውጤት ያላቸው ቢስክሌተኞቿን በሻምፒዮናው እንደምታሳትፍ ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል።

በሻምፒዮናው የወርቅ ሜዳሊያ የሚያገኙ ቢስክሌተኞች በሚቀጥለው ዓመት በሚካሄደው ዓለም አቀፍ የቢስክሌት ውድድር በቀጥታ እንደሚሳሳተፉ ዕድል እንደሚሰጣቸው አስታውቀዋል።

ከአሥር ኪሎ ሜትር እስከ 180 ኪሎ ሜትር የሚሸፍኑ የተለያዩ ውድድሮች እንደሚካሄዱ ታውቋል።

የአማራ ክልል ስፖርት ኮሚሽነር አቶ ባዘዘው ጫኔ በበኩላቸው ሻምፒዮናው በባህርዳር ከተማ መካሄዱ የአገሪቱንና የክልሉን ገጽታ የሚገነባበት ከመሆኑም በላይ፤ ከአፍሪካ ህዝቦች ጋር የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱ የሚያጠናከር መድረክ ይሆናል ብለዋል።

የክልሉ መንግሥትም ለዝግጅቱ ሶስት ሚሊዮን ብር መመደቡንና እንግዶችን ለመቀበል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

እንግዶችን ለሚቀበሉና ለሚያስተባብሩ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችም ስልጠና መሰጠቱን አመልክተዋል፡፡

የከተማዋና የአካባቢዋ ሕዝብ እንግዶቹ እስኪመለሱ በመልካም መስተንግዶ እንዲያስተናግዷቸው ጥሪ አቅርበዋል።

13ኛውን የአፍሪካ ቢስክሌት ሻምፒዮናን ያስተናገደችው የሩዋንዳ ርዕሰ ከተማ ኪጋሊ ነበረች።