የአድዋ ድል ስኬት እያንጸባረቀ ከትውልድ ወደ ትወልድ እንዲተላለፍ ማድረግ ይጠበቅብናል - የአድዋ ድል በዓል ታዳሚዎች

75

አዲስ አበባ የካቲት 23/2011በአጼ ምኒልክ መሪነት የኢትዮጵያ ህዝቦች የአገር አንድነትን ለመጠበቅና ሰላምን ለማረጋገጥ የከፈሉትን መስዋዕትነት ስኬት እያንጸባረቀ ከትውልድ ወደ ትወልድ እንዲተላለፍ ለማድረግ "ጠንክሮ መስራት ይጠበቅብናል" ሲሉ በአዲስ አበባ ከተማ የ123ኛው የአድዋ ድል በዓል ታዳሚዎች አስታወቁ።

ታዳሚዎቹ እንደሚሉት አፄ ምኒልክና ሕዝባቸው የጣሊያንን ጦር ለመግጠም ሲነሱ ዘር ፣ ቀለም ብሔርና ሐይማኖት ሳይለዩ "ምታ ነጋሪት ክተት ሰራዊት በማለት ነው" ለሁሉም ሕዝብ ጥሪ ያስተላለፉት።

በመሆኑም ጥንት ስልጣኔ ባልተስፋፋበት ዘመናዊ መሳሪያና አስተሳሰብ በሌለበት ወቅት አፄ ምኒልክ የኢትዮጵያን አንድነት አስከብረው የማንነት መገለጫችን ለሆነ አኩሪ የአድዋ ድል እንዳበቁን "አሁንም ይሔን ማስቀጠል ይገባናል" ነው ያሉት።

ከቡራዩ የመጣው አቶ ዘላለም ብርሃኑ ''አንድነት እንግዲህ ለኢትዮጵያ  የማያወላዳ ነው። ምኒሊክ መቼም ዳግም መጥተው ወረ ኢሉ ላይ እንገናኝ አይሉንም አዲስ አበባ ላይም ሆነ የትም ቢሆን አንድነት ያስፈልጋል ፤ አንድነት ከሌለ ደግሞ ኢትዮጵያን ልንሰራት ልንገነባት አንችልም የኢትዮጵያ ሕልውና ያለው ደግሞ አንድነቷ ላይ ነው'' ብሏል፡፡

ወጣት ሐይማኖት ተፈራ በበኩሏ  የተከፈለልን ህይወት ቀላል አይደለም አገር በደም መስዋዕት ላይ ነው የፀናችው፤ ወጣቱ ትውልድም ከዚህ መማር ያለበት በወቅቱ ምኒሊክ ከመዝመታቸው በፊት ከንጉስ ጦናና ከአባጁፋር ጋር ተጣልተው ጦርነት አድርገው ነበር፤ ነገር ግን ወደ ጦርነት ሲሔዱ ወንበራቸውን አስረክበዋቸው ነበር የሔዱት ሲመለሱ ያንን ወንበር ይዘውት መጠበቅ ይችሉ ነበር። አቅም ነበራቸው ግን ያንን ያላዳረጉት ግን የአገር አንድነት ይበልጣል ብለው አንድ መሆናቸውም ነው እንድናሸንፍ ያደረገን''ብላለች፡፡

የአድዋ ጦርነት በድል እንዲጠናቀቅና ውጤታማ እንዲሆን እቴጌ ጣይቱን ጨምሮ ከ20 ሺህ በላይ ሴቶች አብረው በመዝመት የነበራቸው አስተዋጽኦ የጎላ መሆኑን የገለፀችው ደግሞ ሌላዋ አስተያየት ሰጪ ወጣት ያብስራ ግርማ፤ አሁንም በተለያዩ የስራ እርከኖች ላይ የተቀመጡ እነዚህ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጠንክረው መስራት እንደሚጠበቅባቸው ተናግራለች።

ሌላው አስተያየት ሰጪ አርቲስትሒሩት ኪሮስ በበኩሏ የሴቶች ተሳትፎ በዚያን ወቅት ስንቅ በማቀበል ሕክምና በመስጠት ከጎናቸው በመቆም ነው። በተለይ እቴጌ ጣይቱ ምን አለች መሰለሽ 'ሴት ነኝ ጦርነት አልወድም በሀገር ከመጣ ግን አይልደራደርም' ብላለች ስለዚህ እኛ ሴቶች የጣይቱ ወኔ ሊኖረን ይገባል።''

ከጥንት አባቶቻችንና እናቶቻቸን ታሪክ እንደምንረዳው "ለጋራ አንድነት፣ሰላም ብልጽግናና እድገት፤ ዘር ፣ቀለምና ብሔር ሳይለየን  ግንባር ቀደም ተሳታፊ መሆን ይገባናል" ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም