ከአድዋ ድል ታሪክ ብሔራዊ መግባባት መማር እንደሚገባ ተመለከተ

95

ጎንደር/ባህርዳር የካቲት 23/2011 ከአድዋ ድል ታሪክ ህዝባዊ አንድነትንና ብሄራዊ መግባባትን መማር እንደሚገባው ተመለከተ፡፡

123ኛውን የአድዋን ድል ምክንያት በማድረግ በጎንደርና በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲዎች  ውይይቶች ተካሄዷል፡፡

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ደሳለኝ መንገሻ በውይይቱ ወቅት እንደተናገሩት  ወጣቱ  በአድዋ ወራሪውን ለማሸነፍ ከቅድመ አያቶቹ የነበረውን የሀገር ፍቅርና  መተማመን አጥብቆ በመያዝ አዲስ ታሪክ ለመስራት መዘጋጀት አለበት፡፡

"የኢትዮጵያን ህዝቦች የማይወክሉ ክስተቶች እየተስተዋሉ ነው" ያሉት ዶክተር ደሳለኝ የእርስ በእርስ ግጭቶችንና በጥርጣሬ መተያየትን በማስወገድ ብሄራዊ መግባባት ሊፈጠር  እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡

የአሁኑ ትውልድ ከአባቶቹ የተረከባትን ኢትዮጵያ ለመጭው ትውልድ ለማስተላለፍ  ከስሜት መውጣትና በምክንያት ማመን እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡

በጎንደር የአባት አርበኞች ማህበር ሰብሳቢ  አቶ ሙሉጌታ አቡሃይ በበኩላቸው "ወጣቱ የህዝብ ፍቅር ኖሮት ሀገሩን በአንድነትና በመተማመን ሊጠብቅ ይገባል" ብለዋል፡፡

ባለፈ ታሪክ መኩራራት  ብቻ ሳይሆን በልማቱ፣ በሰላሙና በፖለቲካው መስክ በትብብርና በመደጋገፍ መስራት እንደሚገባ የገለጹት ደግሞ የጎንደር ሰላምና ልማት ሸንጎ ሰብሳቢ አቶ ባዩ በዛብህ ናቸው፡፡

በውይይቱ  የአሉላ የአደራ ቃል  በሚል መነባንብ ያቀረበው አርቲስት ጌትነት እንየው "የአድዋ ድል ትልቁ ሚስጥር አንድነታችን ነው፤ ሁሉም ዜጋ ከዘረኝነት በመውጣት ሀገሩን የሚጠቅም ስራ መስራት አለበት "ብሏል፡፡

ተማሪ አፈወርቅ ተፈራ በበኩሉ የአድዋን ድል ሲያከብር የጥቁር ህዝቦች ተምሳሌትነት በማሰብ እንደሆነ ገልጿል፡፡

በተመሳሳይ በዓሉ  በባህር ዳር ዩኒቨርስቲ በተከበረበት ወቅት የዩኒቨርሲቲው የታሪክና ቅርስ ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ፕሮፌሰር ሹመት ሲሻኝ እንደገለጹት በአንድ ሀገር ህዝቦች ሲኖሩ በሁሉም ነገር ላይ አንድ መሆን አይችሉም።

"የአድዋ ጦርነት በሚካሄድበት ወቅትም ህዝቦች የየራሳቸው ማንነት ስላላቸው ልዩነቶች ነበሩ፣ ከንጉስ ምኒልክ ጋርም ሳይቀር በሃሳብ ልዩነት ምክንያት አልገብርም የሚሉ አካላት ነበሩ" ብለዋል።

ፕሮፌሰሩ እንዳሉት ሆኖም  በሃሳብና በማንነት ምክንያት ልዩነቶች ቢኖሩም በሀገራቸው ጉዳይ ላይ በምንም ምክንያት ልዩነቶች አይታይባቸውም ነበር።

"በዚህም ምክንያት የመላ አፍሪካ ኩራት ፣የነጮች ወይም  ምዕራባዊያን መሸነፍ እንደሚችሉ ስጋት ያጨረባቸውን ድል መጎናጸፍ ተችሏል" ብለዋል፡፡

የአሁኑ ትውልድ ከቅድመ አያቶቹ የአንድነት ገድል በማስታዋስ ወደ ቀደመ  ኢትዮጵያዊ የአንድነት ታሪክ ለመመለስ ማንበብና አስተሳሰቡን ማስፋት ይጠበቅበታል።

" አዲሱ ትውልድ ኢትዮጵያዊ ነኝ የሚል ስሜትን ዘንግቶ በብሄሩ መመካት መጀመሩን " የገለጹት ደግሞ የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ባህር ዳር ቅርንጫፍ ሊቀመንበር አቶ ዳኝነት አያሌው ናቸው።

ይህንን የተሰሳተ አካሄድ ለማስተካከልና ኢትዮጵያዊነት አስተሳሰብ እንዲጎለበት የታሪክ ምሁራን እውነታውን በሚገባ ማስረዳት የሚችሉ ሰነዶችን ማዘጋጀት እንዳለባቸው አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች መፍትሄ አፈላላጊ ሰብሳቢ ኡስታዝ አቡበከር አህመድ እንዳሉት ወጣቱ  ቅድመ አያቶች በጋራ የሰሩትን ገድል ከመዘከር ባለፈ ወቅቱ የሚጠይቀውን አዲስ የጋራ ታሪክ ለቀጣዩ ትውልድ መስራት ይጠበቅበታል፡፡

ዛሬ በነጻነት ለመናገር የሚያስችል ድል መጎናጸፍ የተቻለው  በተናጥል በተሰራ የድል ታሪክ ሳይሆን ልዩነቶችን በማጥበብ አንድነታቸውን ባገዘፉ ቅድመ አያቶች በጋራ በተገኘ ውጤት መሆኑን ገልጸዋል።

በዓሉን በማስመልከት በሁለቱም ዩኒቨርስቲዎች በተካሄዱት ውይይቶች ተማሪዎችና ሰራተኞች፣ የአባት አርበኞች ፣  አርቲስቶች፣ ምሁራን እና  ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም