ዘመንና ታሪክ

598


በሃብቱ ተሰማ (ኢዜአ)

ታሪክን ማን ይሰራዋል? የሚለው ጥያቄ በዘርፉ ምሁራን አከራካሪነቱ ለዘመናት እንደዘለቀ ነው፡፡ ታሪክ ህዝብ በየዘመኑ የሚከውነው አንዱ የህይወት አካል ነው፤ በሂደት ለተከሰተው ጥሩም ሆነ መጥፎ አጋጣሚዎች ወቀሳውም ሆነ ምስጋናው የግለሰብ ነው ከሚሉ እሳቤዎች እስከ  ህዝብ መሪውን የሚከተል በመሆኑ የክዋኔው ፋናም ለመሪው ሊሰጥ ይገባል የሚሉ የታሪክ ብያኔዎችም አሉ ፡፡

የግለሰብ ድርጊት እየሰፋ የብዙዎች እሳቤ ይሆናል። ብዙዎችንም የታሪኩም አካል ያደርጋቸዋል ለሚለው ሙግትም በርካታ ማሳያዎች ይቀርብበታል። የቅርብ ግዜው የአፍሪካ የታሪክ ክስተት ቱኒዚያዊው ሙሀመድ ቡአዚዝ በህዳር እአአ 17/ 2010 የሀገሪቱን አስተዳደር በመቃወም በአደባባይ ራሱን በእሳት በማጋየት ያቀጣጠለው አብዮት ከሀገሪቱ አልፎ የአረቡን ጸደይ አብዮት እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል፡፡ ራቅ ካሉት ዘመናትም አሜሪካን ከእግሊዞች ቀኝ ግዛት ለማላቀቅ እአአ ከ1755- 1783 በተደረገ ጦርነት ጆርጅ ዋሸንግተን ከፍተኛውን ድርሻ በመያዝ ለአሁኗ አሜሪካ መመስርት መሰረት ጥሎ አልፏል።

ማንዴላ የደቡብ አፍሪካን የጸረ አፓርታይድ በመምራት፣ ማህተመ ጋንዲም  ህንድን ከእንግሊዝ ቀኝ ግዛት ለማላቀቅ በተደረገ ትግል  የቀዳሚነት ሚናን አበርክተዋል፡፡ ከዚህ በተቃርኖ የሚነሳው ደግሞ ታሪክን የሚፈጥረው ሰፊው ህዝብ ነው የሚለው ሃሳብ ነው፡፡ በውስጡም የመሪዎች ሚናና የግለሰብ አስተዋጽኦ ተጣምሮ እንጂ በተናጠል  የሚታይ አይደለም በሚል የሚሞግቱ ብዙዎች ናቸው፡፡ ለአብነትም የአድዋን ተጋድሎና የፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ የታሪክ ክስተቶች ይጠቀሳሉ። መላው ጥቁር ህዝቦች ለመብታቸው መከበር የአድዋን ተጋድሎ ተምሳሌት በማድረግ እአአ በ1960ዎቹ በርካታ የአፍረካ ሀገራት ጸረ ቀኝ ግዛት ትግል አካሂደዋል፡፡

የአፍሪካ የታሪክ ክስተቶች በምሁራን እይታ

መላው ጥቁር ህዝቦች ለመብታቸው መከበር የአድዋን ተጋድሎ ተምሳሌት በማድረግ በ1960 ዎቹ በርካታ የአፍረካ ሀገራት ጸረ ቀኝ ግዛት ትግል አድርገዋል። የጀግኖች አርበኞች ማህበር ምክትል ፕሬዘዳንት አምባሳደር አለማየሁ አበበ እንደሚያስረዱት የአድዋ ተጋድሎ የአድነትና የመተባበር ባህል የጣሊያንን ወራሪ ጦር ድል በመንሳት የሰሩት አኩሪ ታሪክ  ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለመላው ጥቁር ህዝቦች የሞራል ሰንቅ ነው ይላሉ፡፡

ኢትዮጵያውያን በሽምቅ ውጊያ ለሀገር ነጻነት መከበር ያደረጉት ተጋድሎ የቻይናው  የሶሻሊስት  የመጀመሪያ መሪ ማኦ ዜዶንግ፤ ቻይና ከጃፓን ጋር ያደረገችው ጦርነት፤  የኢትዮጵያውን  የአንድነት መንፈስና የጦርነት ስልት  ለህዝብ መቀስቀሻ መጠቀማቸውን አምባሳደር አለማየሁ ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡

የኢትዮጵያ ህዝብ ምንም በኑሮዋቸው ቢጎሳቆሉና በመንግስታቸው ቅሬታ ቢኖራቸውም ለነጻነታቸው በአንድነት ይነሳሉ ያሉት አምባሳደሩ ይሄን መሰል ታሪክ የሚሸረሸሩ  አዝማሚያና እንቅስቃሴን የአሁኑ ትውልድ  በመነጋገር እየፈታ፤  ከታሪክ ሽሚያ ራሱን መቆጠብ እንዳለበት ከረጅም አመት የአርበኝነትና አንባሳደርነት ህይወት ያዩትንና ያሳለፉትን   ልምድ ያካፍላሉ።

ትውልዱ የውጪውን ታሪክ ከመማሩ በፊት የሀገሩን  ታሪክ እንዲያውቅ አላደረግንም ያሉት አምባሳደር አለማየሁ፤ ሁሉም ሰው በተረዳው ልክ ለሀገር ፍቅር ያደረገውን አበርክቶ፣  የጀግኖች አርበኞች ማህበር፣ የትምርት ተቋማትና መንግስትም በተገቢው መንገድ ባለማስተማራቸው  ተወቃሾች  እንደሆኑ ይጠቅሳሉ ፡፡

በተለያዩ ግዜያት የተነሱ ጥያቄዎችና ውጤቱ

በአፍሪካም ሆነ በሀገራችን የተነሱ የዴሞክራሲና የኢኮኖሚ ጥያቄዎች በፖለቲካ ፓርቲዎችና በአምባገነን መሪዎች መነጠቁ ታሪክ ያስረዳል፡፡ ይህን ሀቅ  የሚያስረግጥልን የአፍሪካ ትላልቅ ጸሀፍት በለውጡ መቀልበስ  በተስፋ መቁረጥ የጻፉት ድርሳናት ያሳያሉ፡፡

የጋናው ደራሲ አይኩይ አርማህ  “ቆንጆዎቹ አልተወለዱም” በሚል ርእስ ያስነበበው ጽሑፍ  ለዚህ አንዱ ማሳያ ነው። በሀገራችንም መሰል ታሪኮች  መከሰታቸውን በኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ  የህግና የታሪክ መምህር ዶክተር አልማው ክፍሌ  እንዲህ ብለው ያጋሩናል “በኛ ሀገር ታሪክ ለዴሞክራሲም ሆነ የሀብት ክፍፍል ጥያቄዎች ከተነሱበት አላማ  ይልቅ ለአሁኑ ፖለቲካ ክፍፍልና አለመረጋጋት መሰረት ናቸው”፡፡

የመሬት ላራሹና የትምህርት ጥራት ጥያቄን ውጭ ተምረው የመጡ ምሁራን የውጪውን ተሞክሮ ከሀገራችን ባህል ጋር  ያለመቃኘታቸው ለፖለቲካ ሽኩቻ  መንስኤ እንደሆኑም በማሳያነት ይገልጻሉ፡፡ ችግሩ የአፍሪካም መገለጫ እስኪ መስል ድረስ እአአ ከ1960 እስከ 1970 በርካታ የአፍሪካ ሀገራት ከቀኝ ግዛት ቢወጡም ነጮችን በጥቁር መሪዎች ከመቀየራቸው ባለፈ የዴሞክራሲ አስተሳሰብ ባለመምጣቱ በአህጉሪቱ 193 መፈንቀለ መንግስት መካሄዱን ከታሪክ ያስታውሳሉ ፡፡

እነዚህን ችግሮች ለመፍታት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጭምር  ሀገራቱ መሪዎቻቸውን በምርጫ ብቻ ወደ ስልጣን እንዲያመጡ ቢያስቀምጥም እስካሁን ትርጉም ያለው  ለውጥ  አለመታየቱን የዶክተር አልማው ያስረዳሉ፡፡ የህዝቦችን የዴሞክራሲና የኢኮኖሚ ትግል  ፓርቲዎችና ግለሰቦች  በመቀማት ወደ የአምባገነን ስርአት መለወጣቸው ለተደጋጋሚ ትግል እንደዳረገን የሚያስረዱን ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህር ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና ናቸው፡፡

“የኛ ሀገር ፖለቲካና ኮረንቲ በሩቁ ነው በሚል ብሂል  ጥቂቶች የሚሳተፉበት፤   የሰዎች የመብት ጥያቄ በየግዜው በፓርቲዎችና አምባገነን መሪዎች በመጠለፉ ከፖለቲካ ፍጆታ ባለፈ ለውጥ አልመጣም” ይላሉ ፕሮፌሰር መረራ፡፡

የመብት ጥያቄን ይዘው ወደ ፊት ከወጡትም የተማሩ ሰዎች የዴሞክራሲ ባህልን ጠንቅቀው ባለመረዳት  ከመቻቻልና የልዩነት ሃሳብን ከማስተናገድ ይልቅ የኔ ብቻ ይደመጥ አስተሳሰብ በማዳበራቸው ለአሁኑ አለመደማመጥና አልሸነፍ ባይነት አጋልጦናል ነው  ያሉት ፕሮፌሰሩ። 

ያለፉበትን የፖለቲካ እንቅስቃሴም ሲቃኙ “በኛ ዘመን ወጣቶች በተማሪዎች ንቅናቄ ቢሳተፉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ሚናቸውን ወስደውታል፤ ከነሱም የወታደሩ መንግስት ቀምቷል፤ በኢህአዴግም ወጣቶች ያላቸውን አቅም አልተወጡም” የሚሉት ፕሮፌሰር መረራ ወጣቶች ለለውጥ ትልቁን አቅም ቢያበረክቱም በአንጋፋዎቹ አላማውን እየሳተ መሄዱንም ታሪክን እያጣቀሱ ይናገራሉ።

የህዝብ ትግልና ታሪክ

መሪዎች  አምባገነን ሲሆኑ ተው የሚል የሀገር ሽማግሌ፣ የእምነት አባቶች እንዲሁም የመላው ህዝብ ትግል አስፈላጊ ነው፡፡ ይህን ባለመቀበል ህዝባቸውን ለስደት ሀገራቸውንም  ለድህነት የዳረጉ በርካታ ሀገራት  እንደ ነበሩ ከኋላው ታሪክ መረዳት ይቻላል። በሌላ በኩል  ሀገርን  በመምራት በሚከሰቱ ስህተት መንግስታት ራሳቸውን ተጠያቂ አድርገው ስልጣናቸውን ለቀዋል፡፡ ከአፍሪካ  የግብጹ መሪ ገማል አብደል ናስር በእስራኤልና ግብጽ የስድስት ቀን ጦርነት ለደረሰው ጉዳት ሀላፊነቱን ወስደው ስልጣናቸውን ለመልቀቅ  ያቀረቡት ጥያቄ  ህዝቡ በታላቅ ሰላማዊ ሰልፍ ወደ ስልጣን እንዲመለሱ ማድረጉ በአብነት የሚጠቀስ ነው።

በኛም ሀገር በወርሀ የካቲት 2010 ዓ.ም የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በመልካም አስተዳደር ጉድለት፤ ሌሎች ህዝቡ በመንግስት ላይ ያለው ጥያቄ በመበራከቱና እዚህም እዚያም የሰላም  እጦት በመከሰቱ ለሰላሙ አርዓያ  ለመሆን ሀላፊነታቸውን ለመልቀቅ ጥያቄ ማቅረባቸው የቅርብ ግዜ ትዝታችን ነው።

ታሪክ ሰሪው ሰፊው ህዝብ በመሆኑ በየግዜው የተፈጠሩ መልካምና አሳዛኝ የታሪክ ሁነቶች  እንዲሁም የታሪክ ሽሚያ  ከመፍጠር አልፎ የኔብቻ ይደመጥ እሳቤ በእስካሁኑ ጉዞዋችን አብሮን ያለ ባህሪ  ነው። የህዝብ ያለፈ ሁለንተናዊ መስተጋብር ውጤት በመሆኑ ለአሁኑ  መማሪያና ለመጪውም አቅም ነው በማለት ዶክተር አልማው የሚገልፁት፡፡

ታሪክ የሚጻፈው  መረጃዎችን በማደራጀትና ምርምርን በማድረግ  ቢሆንም በእውቀት ማነስ፣ በግል ፍላጎት  ወይም በተለየ ገፊ ምክንያቶች በተሳሳተ መንገድ ታሪክ መጻፉ ሀገርን ወደ አልተፈለገ አቅጣጫ ይወስዳል ያሉት ዶክተር አልማው፤ ካለፈው ታሪክ  ተምረን ዛሬን የምንሰራበት፤ ለትውልድም ክፋትን ሳይሆን ብልጽግናን የምናሻግርበት ሊሆን ይገባል ሲሉ ምክራቸውን ይለግሳሉ።

የታሪክ ክስቶች በትውልድ ቅብብሎሽ

ሁሉም ትውልድ ለሀገሩ እድገትና ለነጻነት የከፈለው መስዋትነት ትልቅ ዋጋ አለው፡፡ አንዳንድ ወቅቶች ወይም ወራቶች በሀገር ታሪክ ውስጥ ሰፊ ቦታ አላቸው፤ በተለይም በሀገራችን የተደረጉ ጦርነቶች ለሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገራት ተጽእኖአቸው ጉልህ መሆኑን ምሁራንና በታሪኩ ውስጥ ያለፉት ጀግኞች አርበኞች ከታሪክ ማህደር ይጠቅሳሉ፡፡

በሀገራችን የነጻነት ተጋድሎ ሀገራችንን ከሶስት ሺ አመት በላይ  በነጻነት ያቆዩት  ጀግኖች አርበኞች  ብቻ ሳይሆኑ የሁሉም ህዝብ ተሳትፎ መሆኑን የነገሩን ደግሞ አምባሳደር አለማየሁ አበበ የጀግኖች አርበኞች ማህበር ምክትል ፕሬዘዳንት ናቸው፡፡

እንዳሁኑ የተደራጀ ጦር ሰራዊትና የጦር መሳሪያ በሌለበት  “በሀገር በቀል ጦር መሳሪያ ዳር ድንበር በማስከበራቸው ህዝቡ ትልቅ ምስጋና ይገባቸዋል” ያሉት አምባሳደር አለማየሁ በተለይ ህዝብን በአንድነት በማንቀሳቀስ በዘመናቸው የከፈሉትን መስዋዕትነት  በአርአያነት ማስቀጠል የትውልዱ ኃላፊነት ነው፡፡

ሁሉም ትውልድ የራሱ ታሪክና የሀገር ግንባታ አሻራ አለው የሚሉን ዶክተር አልማው  ይህን በእውቀት መዝግቦ በማስቀመጥ  ረገድም  በርካታ ጉድለቶች አሉ ይላሉ። የተጻፉትም ሰነዶች ቢሆኑ ለገድሎች የሚቀርቡ በመሆናቸው በኢትዮጵያ የታሪክ ጽሑፎች ውስጥ ታሪካችን አልተካተተም የሚሉ  ትርክቶች አሉ፡፡ በተካተቱትም ቢሆን በተገቢው የአልተገለጽንም  የሚል ቅሬታ የሚያቀርቡ ብዙዎች ናቸው። የዘርፉ ምሁራንም  እነዚህን ሀቆች እንደሚጋሩት ዶክተር አልማው ይናገራሉ።

ታሪክ ሰሪው ሰፊው ህዝብ በመሆኑ ካለፈው ስህተት በመማር ለመጪው ጊዜ በጋራ የምንሰንቅበት እንጂ የእርስ በርስ መቆራቆሻ መሆን የለበትም በማለትም ዶክተር አልማው ምክራቸውን ለግሰውናል። ሁሉም ትውልድ ለሀገሩ እድገትና ለነጻነት የከፈለው መስዋዕትነት ትልቅ ዋጋ አለው። በሀገራችን ታሪክም ወራቶች የተለያዩ ክስተቶችን ያሳለፉ ቢሆንም በተለይ የካቲት ወር  ስነሳ በርካታ ክስተቶችን እናስታውሳለን፤ ያለፈ ታሪክም ይሄንኑ ይመሰክራል።

የካቲት ወር በኢትዮጵያ ታሪክ

በኢትዮጵያ ወርኃ የካቲት ስታወስ ለጥቁር ህዝቦች ነጻነት መሰረት የተጣለበት ነው። በወርሃ የካቲት ከነበሩ ድሎች የተወሰነውን ለማንሳት ያህል  ሀገራችን የጣሊያን ወረራን በአድዋ፣ የሶማሊያ ጦርነትን በካራማራ  ድል የተቀዳጀችበት ነው፡፡ የካቲት 12 – የሰማዕታት ቀንና ህወሀትም  የደርግ ስርአትን በመቃወም የተነሳበት ወር መሆኑ ማሳያዎች ናቸው።  

ወርኃ የካቲት ገበሬዎች በአጼ ኃይለሥላሴ ላይ አምጸዋል፤ መምህራንን፣ ተማሪዎችን፣ አሽከርካሪዎችን፣ የመንግስት ሠራተኞችን፣ የእስልምና ሐይማኖት ተከታዮችንና ወታደሮችን ለተቃውሞ ወደ አደባባይ አስወጥቷል። ሕዝባዊ አብዮትም ቀስቅሷል። ደርስጌ ላይ አጼቴድሮስ የነገሱትም በዚሁ ወር ነው፡፡

የአድዋ ድል ልዩ ገጽታ

የአድዋ ድል ስታወስ ይላሉ በኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ  የህግና የታሪክ መምህር ዶክተር አልማው ክፍሌ፤ “በእስማኤል ፓሻ ተመርቶ ከመጣው የግብጽ ጦር፣ ጉራና ጉንዲት ቦጎስ፣ ከሶማሊያን ጋር ከተደረጉና  ከሌሎች ጦርነቶች  የአድዋን ድል  ጉልህ የሚያደርገው በታሪክ መስፈርቶች ነጭ በጥቁር መሸነፉ አዲስና የመጀመሪያ ታሪክ አድርጎታል”።

አድዋ ድል የአለምን የጦር ስልት ከጦር መሳሪያ ወደ ስነ ልቦና እንዲቀየር ማድረጉ፣ ቀጣይነት ያለው ተጽኖ ፈጣሪ ሆኖ ኢትዮጵያን የአለም  ትኩረት ማድረጉ፤ ለመላው አለም የነጻነት ትግል አርአያ መሆኑና   ለፓን አፍሪካኒዝም መመስረት ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ያነሳሉ ዶክተር አልማው፡፡ 

እአአ በ1904 ጃፓኖች ራሺያን ለመውረር ሲነሱ የአድዋ ድል ስልትን በአርዓያነት ተጠቅመውበታል ያሉን ዶክተር አልማው፤ ለውለታዋም ጃፓን በርካታ ኢትዮጵያውያንን ማስተማሯ፤ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያንም በብዙ ሀገር እንዲገነባና ባንዲራዋም የነጻነት ምልክት እንዲሆን  የአድዋ ድል መነሻ መሆኑንም የታሪክ ምሁሩ ያስረዳሉ።  በየዘመኑ የነበሩ የታሪክ ትሩፋቶች ለታለመላቸው ዓላማ እንዲውሉ ትላልቆቹ በማስተማርና ታሪክን ወደ ቀጣየሁ ትውልድ በማሻገር ለሀገር አንድነትና እድገት ልንጠቀምበት ይገባል የእለቱ መልዕክታችን ነው።