በማህበረሰብ የጤና መድህን ፕሮግራም ከ16 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ተጠቃሚ ሆነዋል - የኢትዮጵያ ጤና መድህን አጀንሲ - ኢዜአ አማርኛ
በማህበረሰብ የጤና መድህን ፕሮግራም ከ16 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ተጠቃሚ ሆነዋል - የኢትዮጵያ ጤና መድህን አጀንሲ

መቀሌ ግንቦት 22/2010 በማህበረሰብ የጤና መድን ፕሮግራም ከ16 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ተጠቃሚ መሆናቸውን የኢትዮጵያ ጤና መድህን አጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አስታወቁ፡፡ የፕሮግራሙ ተጠቃሚዎች በበኩላቸው በሚያዋጡት አነስተኛ ገንዘብ በቂ የህክምና አገልግሎት ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡ በትግራይ ክልል ውቅሮ ከተማ በተዘጋጀ የውይይት መድረክ ላይ የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ አታኽልቲ አብርሃ እንደገለፁት የማህበረሰብ ጤና መድን አገልግሎት በአገሪቱ በሚገኙ 384 ወረዳዎች ለሙከራ ተግባራው በመደረግ ላይ ነው፡፡ በእነዚሁ ወረዳዎች የሚገኙ ከ16 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የኘሮግራሙ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉንም ገልፀዋል፡፡ ፕሮግራሙ በተተገበረባቸው ወረዳዎች የህብረተሰቡ የጤና አገልግሎት አጠቃቀም እየተሻሻለ ከመምጣቱም በላይ የእርስ በርስ የመደጋገፍ ባህሉ እየጎለበተ እንዲመጣ እያስቻለ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በቀጣይም የጤና መድህን ሽፋኑን የመንግስት ሠራተኞችን ጨምሮ በሁሉም የሃገሪቱ ክፍሎች ለማዳረስ የህዝብ ንቅናቄ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውንም አስታውቀዋል፡፡ በአንዳንድ ጤና ተቋማት የአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን ለመሙላት ኤጀንሲው ከፌደራል ጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና ባለድርሻ አካለት ጋር ተቀናጅቶ እየሰራ እንደሆነም ተናግረዋል። የታህታይ ማይጨው ወረዳ ነዋሪ አቶ ጀማል ካሕሳይ ፕሮግራሙን አስመልክተው እንዳሉት፣ የጤና መድህን አባል በመሆናቸው በየዓመቱ በሚያዋጡት አነስተኛ ገንዘብ ራሳቸውና ቤተሰባቸውን ከበሸታ መታደግ ችለዋለ። በየዓመቱ በሚከፍሉት 180 ብር የአባልነት መዋጮ የአንጀት በሽታ አጋጥሟቸው በተደረገላቸው ምርመራ የ4ሺህ ብር ያህል ወጪ በጤና መድህን አገልግሎቱ እንዲሸፈን መደረጉንና ያለምንም ስጋት ከበሽታው መዳናቸውን ገልጸዋል። በትግራይ ምስራቃዊ ዞን የሓውዜን ወረዳ ነዋሪ ወይዘሮ አልማዝ ገብረ ህይወት በበኩላቸው በዓመት አንዴ በሚከፍሉት አነስተኛ የአባልነት ክፍያ እሳቸውን ጨምሮ ቤተሰቦቻቸውን በማሳከም ከከፍተኛ ወጪ እየታደጋቸው መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ‘‘በሽታ መቼ እንደሚከሰት አይታወቅም። በማህበረሰብ ጤና መድህን ፕሮግራም የምከፍለው ገንዘብ ግን ከሌሎች አባላት ጋር ተደጋግፈንና ተጋግዘን በመታከም ተጠቃሚ እያደረገን ነው'' ብለዋል። ላለፉት ሁለት ቀናት በማህበረሰብ የጤና መድን ፕሮግራም አፈፃፀምና ቀጣይ አቅጣጫ ዙሪያ በውቅሮ ከተማ በተካሄደው የውይይት መድረክ ላይ በትግራይ ክልል በየደረጃው የሚገኙ አመራር አካላት፣ የአርሶ አደሮች ተወካዮችና በዘርፉ አፈፃፀም ሞዴል የሆኑ አካላት ተሳትፈዋል፡፡