በኢትዮጵያ የተጀመረውን ለውጥ የሚደግፍ የአሜሪካ የልማት ተቋም መርሃ ግብር ሊጀመር ነው

744

አዲስ አበባ የካቲት 22/2011 በኢትዮጵያ እየተከናወኑ ያሉ የሪፎርም ስራዎችን የሚደግፍ የአሜሪካ የልማት ተቋም መርሃ ግብር ሊጀመር መሆኑን የገንዘብና ኢኮኖሚ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የሚኒስቴሩ የስራ ሃላፊዎች ከአሜሪካው ‘ሚሌኒየም ቻሌንጅ ኮርፖሬሽን’ ሃላፊዎች ጋር ውይይት አካሂደዋል።

ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ ከውይይቱ በኋላ በሰጡት መግለጫ ላይ እንደተናገሩት፤ የሚሌኒየም ቻሌንጅ ኮርፖሬሽን ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በትብብር ለመስራት የሚያስችል መርሃ ግብር ሊጀምር ነው።

ተቋሙ በለውጥ ሂደት ውስጥ ለሚገኙና ከአሜሪካ ጋር ስትራቴጂክና ጠንካራ ወዳጅነት ላላቸው አገሮች ድጋፍ የሚሰጥ እንደሆነም ጠቁመዋል።

መርሃ ግብሩ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አማካኝነት እየተካሄዱ ያሉ የምጣኔ ሀብታዊ፣ ፖለቲካዊና ዲሞክራሲያዊ ማሻሻያዎች የተገኘ ውጤት መሆኑንና አሜሪካ ጠንካራ ደጋፊ መሆኗን ያሳየችበት እንደሆነ ተናግረዋል።

አቶ አህመድ እንደገለጹት፤ የመርሃ ግብሩ የመጀመሪያ ምዕራፍ በቅርቡ ወደስራ ይገባል።

የመርሃ ግብሩ መጀመር ተቋሙ በኢትዮጵያ የተጀመረው ዘርፈ ብዙ ለውጥ ዘላቂነት ላይ አሜሪካ እምነት እንዳሳደረች የሚያሳይ ስለመሆኑም ገልጸዋል።

በቀጣይም  ብዙ ሀብት ሊያመጣ የሚችለውን ዋናው የእርዳታ መርሃ ግብር ተግባራዊ እንዲሆን የዝግጅት ስራ እንደሚሰራም አቶ አህመድ ተናግረዋል።

በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ፍጹም አረጋ በበኩላቸው የመርሃ ግብሩ የመጀመሪያ ምዕራፍ ወደ ዋናው መርሃ ግብር በፍጥነት ማሸጋገር እንዲቻል በቅርቡ የተቋሙ የቴክኒክ ቡድን ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጡ ገልጸዋል።

የሚሊኒየም ቻሌንጅ ኮርፕሬሽን ዋና ሀላፊ ሲንቲያ ሀንገር ተቋሙ የፖሊሲና የተቋዋሚ ለውጦች ላይ በማተኮር ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ምጣኔ ሀብታዊ ዕድገትና ድህነት ቅነሳ ላይ እንደሚሰራ ገልጸዋል።

በኢትዮጵያም መርሃ ግብሩን ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችል አካላት መኖራቸውን አምናለሁ ብለዋል።

በሚቀጥለው ሳምንት መርሃ ግብሩን ለመጀመር ከተቋሙ የሚመጣ ቡድን ወደ ኢትዮጵያ እንደሚገቡም ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ማይክል ሬይነር ኮርፖሬሽኑ ኢትዮጵያን መምረጡ ተገቢ መሆኑንና አሜሪካ በኢትዮጵያ እየተካሄደ የሚገኘውን ለውጥ መደገፏን የሚያሳይ መሆኑን ተናግረዋል።

ተቋሙ በአጋርነት ለመስራት አገሮችን በጥንቃቄ እንደሚመርጥ ገልጸው ድህነትን ለማጥፋት ያለ ቁርጠኝነት፣ የግሉን ሴክተር በሙሉ አቅም መደገፍና መልካም አስተዳደርን ማስፈን ዋነኛ የመምረጫ መስፈርት ስለመሆናቸው ጠቁመዋል።