ለህዳሴ ግድብ ገቢ ለማሰባሰብ የተዘጋጀው ውድድር እክል ገጠመው

705

አዲስ አበባ የካቲት 22/2011 ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ መሰረት የተጣለበትን ስምንተኛ ዓመት አስመልክቶ በአዲስ አበባ በተዘጋጀ የእግር ኳስ ውድድር ላይ በደጋፊዎች መካከል በተነሳ ግጭት ጉዳት ደረሰ።

ውድድሩ በግድቡ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሄራዊ ምክር ቤት እና በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ትብብር ለግድቡ ግንባታ ገቢ ለማሰባሰብ ለስድስተኛ ጊዜ የተዘጋጀ ነው።

ኢትዮጵያ ቡና እና ሲዳማ ቡና እንዲሁም ቅዱስ ጊዮርጊስ እና አዳማ ከነማ በአዲስ አበባ ስታዲዮም ታጋጣሚ ክለቦች ነበሩ።

የመጀመሪያው የመክፈቻ ጨዋታ በኢትዮጵያ ቡና እና በሲዳማ ቡና መካከል ሲካሄድ ኢትዮጵያ ቡና በ12ኛው ደቂቃ ሲዳና ቡና ደግሞ በ32ኛው ደቂቃ ባስመዘገቡት ግብ የመጀመሪያው አጋማሽ 1 ለ 1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቅቋል።

ይሁንና ጨዋታው ሙሉ በሙሉ ሳይጠናቀቅ በኢትዮጵያ ቡና እና በቀጣዩ ጨዋታ ተጋጣሚ ቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች መካከል በተፈጠረ ግጭት ጨዋታው ሲቋረጥ ደጋፊዎች ላይም ጉዳት ደርሷል።

የሁለቱን ቡናዎች ጨዋታ ውጤት በተመለከተ የፌዴሬሽኑ እና የአዘጋጅ ኮሚቴው ውሳኔ የሚጠበቅ ሲሆን የቅዱስ ጊዮርጊስና የአዳማ ከነማ ጨዋታ ከነገ በስቲያ እንዲካሄድ ተወስኗል።