የፌደራሉ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ በአቶ ቴዎድሮስ አዲሱ ላይ ክስ መሰረተ

74

አዲስ አበባ የካቲት 22/2011 የፌደራሉ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ በአቶ ቴዎድሮስ አዲሱ/ቴዲ ማንጁስ /ላይ ክስ መሰረተ።

ጠቅላይ አቃቤ ሕግ 1ኛ አቶ አብዲ ዩሱፍ መሐመዶ/ያልተያዙ/ ፣2ኛ አቶ ቴዎድሮስ አዲሱ፣ 3ኛ አቶ መሃመድ አሕመድ /ያልተያዙ/፣ 4ኛ አቶ አብዱላሂ ሁሴን /ያልተያዙ/ በ15 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ የሙስና ወንጀል ክስ መስርቶባቸዋል።

1ኛ ተከሳሽ ሕዝባዊ ድርጅት በሆነው የኒያላ ኢንሹራንስ ጂግጂጋ ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ፣ 2ኛ ተከሳሽ በግል የሶማሌ ፕሪንቲንግ ፕሬስ ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ፣ 3ኛ እና 4ኛ ተከሳሾች ደግሞ እንደቅደም ተከተላቸው የሱማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ትምህርት ቢሮ ኃላፊና የፋይናንስና ሎጂስቲክስ የስራ ሂደት ባለቤት የነበሩ ናቸው።

አቃቤ ሕግ ለፍርድ ቤቱ 15ኛ ወንጀል ችሎት ያቀረበው ክስ እንደሚያመለክተው የሱማሌ ክልል ትምህርት ቢሮ ከሶማሌ ፕሪንቲንግ ፕሬስ ባለቤት አቶ ቴዎድሮስ አዲሱ ወይም ሁለተኛ ተከሳሽ ጋር ለመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች 578ሺህ 274 መጽሃፍትን ከ18 ነጥብ 9 ሚሊዩን ብር በላይ ወጪ አሳትሞ ለማቅረብ ውል ገብቷል። 

ሆኖም ስራው በውሉ መሰረት ሳይከናወን የቀድሞ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ከኒያላ ኢንሹራንስ አክሲዩን ማሕበር ጅግጀጋ ቅንጫፍ ሥራ አስኪያጅና ከክልሉ የቀድሞው ትምህርት ቢሮ የፋይናንስ ሎጂስቲክስ የሥራ ሂደት ኃላፊ ጋር በመመሳጠር የቅድሚያ ክፍያ ዋስትና ያለአግባብ እንዲከፈለው ማደረጉን ያመለክታል።

በዚህ መሰረትም 1ኛ ተከሳሽ በፌዴራል መንግስት በተመዘገበ ሕዝባዊ ድርጅት ኒያላ ኢንሹራንስ አሰራርና መመሪያ ውጭ ያለ አግባብ ዋስትና በመስጠት፣ 3ኛ እና 4ኛ ተከሳሾችም ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎች ሆነው ሲሰሩ ለ2ኛ ተከሳሽ አቶ ቴዎድሮስ አዲሱ 15 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር በላይ ክፍያ እንዲፈፀም አድርገዋል። ገንዘቡ እንዲመለስና መጽሐፍቱም እንዲገቡ ባለማድረግ ወንጀል ነው የተከሰሱት። 

ከዚህም ሌላ 2ኛ ተከሳሽ ከመንግስትና ሕዝባዊ ድርጅት ኃላፊዎች ጋር ተመሳጥሮ ያለአግባብ ዋስትና እንዲሰጠው አድርጎ ክፍያ በመውሰዱ መጽሐፍቱንም ባለማቅረቡ በሕዝብና በመንግስት ገንዘብና በመማር ማስተማር ሂደት ላይ ክፍተኛ ጉዳት ማድረሳቸውም በክሱ ላይ ተመልክቷል። 

በመሆኑም 1ኛ፣ 3ኛ እና 4ኛ ተከሳሾች የመንግሰትንና የሕዝባዊ ድርጁቶች ስራዎችን በማይመች አካሄድ በመምራት፤ 2ኛ ተከሳሽ ደግሞ በመንግስትና በሕዝባዊ ድርጅት ሰራተኞችና ኃላፊዎች በሚፈፀም የሙስና ወንጀል ልዩ ተካይፋ በዋና ወንጀል አድራጊነት ተከሰዋል።

ሁለተኛ ተከሳሽ አቶ ቴዎድሮስ አዲሱ ደግሞ በሶማሌ ክልል ከሐምሌ 28 እስከ 30 ቀን 2010 በነበረው ግርግርና ሁከት እጃቸው አለበት ተብለው በመጠርጠራቸው በቁጥጥር ስር ውለው ነበር።

ሆኖም ፍርድ ቤቱ በ80 ሺህ ብር ዋስ እንዲለቀቁ አዞ እንደነበርም ይታወሳል።

በመጨረሻም ፍርድ ቤቱ ያልተያዙ ተከሳሾችን ፖሊስ በቁጥጥር ስር አውሎ እንዲያቀርብ ለመጠበቅ ለመጋቢት 20 ቀን 2011 ዓም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቶዋል።

ፍርዱ ቤቱም አቶ ቴዮዎድሮስ አዲሱ የቀረበባቸውን ክስ በንባብ እንዲያሰሙ ያደረገ ሲሆን መቃወሚያቸውንም ለየካቲት 20 ቀን 2011 እንዲያቀርቡ ቀጥሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም