የዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር 17ኛ መደበኛ ጉባዔውን ጀመረ

83

ሰቆጣ  ካቲት 22/2011 የዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ምክር ቤት 17ኛ መደበኛ ጉባዔውን ማካሄድ ጀመረ፡፡

ምክር ቤቱ በዛሬው ውሎው የበጀት ዓመቱን የስድስት ወራት የአፈጻጸም ሪፖርቱን እየገመገመ ነው፡፡

የአስተዳደሩ ዋና አስተዳዳሪ አቶ በሪሁን ኪዳነ ማሪያም ሪፖርቱን ባቀረቡበት ወቅት እንዳሉት አስተዳደሩ በግማሽ ዓመቱ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመፍታት ጥረት አድርጓል።

በዞኑ በ2010/2011 የምርት ዘመን ለመሰብሰብ ከታቀደው ከሁለት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ኩንታል ምርት ውስጥ 674 ሺህ  ኩንታል  ተሰብስቧል።ምርቱ ከዕቅዱ በታች የተሰበሰበው የምርት ግብዓቶች በበቂ መጠን ባለመቅረባቸው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

የምግብ ዋስትና እጥረት ላለባቸው ውስጥ 127ሺህ የሚሆኑ ወገኖች በማህበራዊ ልማት ተሳተትፈው ተጠቃሚ መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡

ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ 12ሺህ ህጻናት በትምህርት ገበታ ላይ እንደሚገኙ ዋና አስተዳዳሪው አስታውቀዋል፡፡

የተቀናጀ ተግባር ተኮር የጎልማሶች ትምህርትና የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድን አገልግሎት አፈጻጸም በዝቅተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኙም ገልጸዋል።

የአስተዳደር ምክር ቤቱ ዋና አፈ ጉባዔ አቶ ኃይሉ ሚሰው በበኩላቸው የአስተዳደሩ አስፈፃሚ አካላት በሪፖርት በቀረበውና በቋሚ ኮሚቴዎች የመስክ ምልከታ የታዩ ክፍተቶችን ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩበት አሳስበዋል፡፡

በአስተዳደሩ ያለውን ሀብት በማስተዳደርና ውጤታማ በሆነ መንገድ እንዲጠቀሙበትም ጠቁመዋል።

የምክር ቤቱ አባላት ከሕዝብ በተደጋጋሚ የሚነሱ የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት እንዲረባረቡ ጠይቀዋል፡፡

አስተዳደሩ የዝናብ አጠር አካባቢ በመሆኑ በምግብ ዋስትና ራሱን ባለመቻሉና ሕጻናት ትምህርታቸው በማቋረጥ ለተረጂነት፣ ለስደትና ለልመና የሚዳርጉበት ሁኔታን ለመቀየር  ዘላቂ መፍትሄ መሻት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

ምክር ቤቱ በሶስት ቀናት ቆይታው የውስጥና የውጭ ኦዲት ግኝት ሪፖርት፤የትምህርት ጥራት እንዲሁም የከፍተኛ ፍርድ ቤት አፈጻጸም ሪፖርት ቀርቦ ይገመግማል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም