የአሜሪካው ሚሌኒየም ቻሌንጅ ኮርፖሬሽን ኢትዮጵያን ጎበኘ

65

አዲስ አበባ የካቲት 22/2011 የአሜሪካው ሚሌኒየም ቻሌንጅ ኮርፖሬሽን ልዑካን ቡድን በኢትዮጵያ ምጣኔ ኃብታዊ እድገት ከመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ጋር ለመመካከር በኢትዮጵያ ጉብኝት አደረገ።

የአሜሪካ ኤምባሲ ለኢዜአ በላከው መግለጫ "በኮርፖሬሽኑ ምክትል ፕሬዚዳንት ሳይንቲያ ሁገር የሚመራው ልዑክ ቡድን ትላንትና ዛሬ ጉብኝቱን አድርጓል።

በቆይታቸውም ከመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፤ ከግል ባለኃብቶችና ከሌሎች የልማት ማኅበረሰቦች ጋር በመገናኘት ምክክር አድርገዋል።

በውይይታቸውም በኢትዮጵያ ምጣኔ ኃብት ዘርፍ አዲስ የእድገት መርኃ ግብር ለመፍጠር በሚያስችሉ ጉዳዮች ትኩረት ማድረጉን ነው መግለጫው ያስረዳው።

የኮርፖሬሽኑ ምክትል ፕሬዚዳንት ሳይንቲያ ሁገር "ኢትዮጵያ ከኮርፖሬሽኑ ጋር መሥራቷ  ለዴሞክራሲና ለምጣኔ ኃብት እድገት ያላትን ጽኑ ቁርጠኝነት ያሳያል" ነው ያሉት።

አዲሱ ትብብር ሁለቱ አገራት ያሏቸውን እሴቶች ለማጠናከርና በተለይም ምጣኔ ኃብታዊ እድገት ለማምጣት የሚያደርጉትን አጋርነት ያጠናክረዋል ብለዋል።

በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ሚካኤል ራይኖር በበኩላቸው ጉብኝቱ አሜሪካ ኢትዮጵያ የጀመረችውን የማሻሻያ ሥራዎች ከግብ ለማድረስና ዘላቂ ለማድረግ ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳይ መሆኑን ነው የገለጹት።

ኢትዮጵያ ከኮርፖሬሽኑ ጋር በጋራ በምትሰራባቸው ጊዜያት የኢትዮጵያን ምጣኔ ኃብታዊ እድገት በጥምረት እየገመገሙ ቀጣይ አቅጣጫዎችን ያስቀምጣሉ ተብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም