በአደንዥ ዕጽ ዝውውርና ሌሎች ወንጀሎች የተጠረጠሩ 47 ኢትዮጵያዊያን በቻይና ታስረዋል - የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

65

አዲስ አበባ 22 / 2011 በአደንዛዥ ዕጽ ዝውውርና ሌሎች ወንጀሎች የተጠረጠሩ 47 ኢትዮጵያዊያን በቻይና መታሰራቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለፀ።

ኢትዮጵያዊያኑ በግድያ፣ በስርቆትና በሳይበር ወንጀል እንደዚሁም ያለ ቪዛ ወይንም ያለመኖሪያ ፍቃድ ረዥም ጊዜ በቻይና መቆየትና ያለ ሥራ ፈቃድ በመሥራት ወንጀል ጭምር ነው ለእስር የተዳረጉት።

የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አቶ ነብያት ጌታቸው ዛሬ በሰጡት መግለጫ በአደንዛዥ ዕጽ ዝውውር ወንጀል ተጠርጥረው ለእስር የተዳረጉት ኢትዮጵያዊያን ባለማወቅ ሰዎችን ለመተባበር ብለው በተቀበሉት ሻንጣ ውስጥ በህገ-ወጦች የተደበቁ እጾች በመገኘታቸው ነው።

ከእነዚህም መካከል የተወሰኑት በተጠረጠሩበት ወንጀል ተፈርዶባቸው የእርምት ጊዜያቸውን እየተከታተሉ ሲሆን ቀሪዎቹ ደግሞ ጉዳያቸው  በምርመራ ላይ እንደሆነም ገልጸዋል።

ሚኒስቴሩም ቤጂንግ በሚገኘው ኤምባሲና ቆንጽላ ጽህፈት ቤቶች አማካይነት ጉዳዩን እየተከታተለ መሆኑን አንስተዋል።

ጎን ለጎንም በሕገ-ወጥ አካላት በሚቀርቡ ነጻ የትምህርት እድል በርካታ ኢትዮጵያዊያን ዜጎች በስህተት ወደ ቻይና ካቀኑ በኋላ ከፍተኛ መጉላላት እየገጠማቸው ነውም ብለዋል።

በሌላ በኩል ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከጂቡቲ ወደ የመን በሕገ-ወጥ መልኩ የሚጓዙ ተጓዦችን ለመከላከል ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተቀናጅቶ እየሰራ እንደሆነም ቃል አቀባዩ ጠቁመዋል።

ይህንን ሕገ-ወጥ መንገድ በመከተል ወደ የመን የሚያቀኑት ኢትዮጵያዊያን ቁጥር በወር እስከ 12 ሺ እንደሚደርስ ነው የገለፁት። 

በዚህ ሣምንት በተለያዩ ችግሮች ውስጥ የነበሩ 1 ሺህ 40  ኢትዮጵያዊያን ከሳኡዱ አረቢያ እንዲሁም 1 ሺህ 415  ደግሞ ከፑንትላንድ ወደ አገራቸው መመለሳቸውን ተናግረዋል።

በቀጣይም አገራቱ ከዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት ጋር በመተባበር ከ1 ሺህ በላይ ዜጎችን ወደ አገር ቤት ለመመለስ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በጂቡቲ የተካሄደው 46ኛው የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ-መንግሥታት ባለሥልጣን (ኢጋድ) ስብሰባ በቀጣናው የጂኦ-ፖለቲካል ችግሮችን ለመቋቋም የሚያስችል አቅጣጫ አስቀምጧል ብለዋል።

ኢጋድ የጀመረውን ቀጠናው ምጣኔ ኃብታዊ ትስስር ለማጠናከረ የሚያስችል መዋቅራዊ ለውጥ ለማድረግም በስብሰባው አባል አገራቱ የጋራ ስምምነት ላይ መድረሳቸውንም ቃል አቀባዩ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም