ወርሃዊው የእግር ጉዞ ዜጎች እየተስፋፋ ለመጣው ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ትኩረት እንዲሰጡ ያግዛል

284

አዲስ አበባ  የካቲት 222011 አውራ ጎዳናዎችን  ከተሽከርካሪ እንቅስቃሴ ነጻ በማድረግ የነዋሪውን በእግር የመጓዝ ልምድ ለማጎልበት የተጀመረው መርሃ ግብር በአገሪቱ እየተስፋፋ የመጣውን ተላላፊ ያልሆኑ የጤና ችግሮችን ለመከላከል ያግዛል ተባለ። 

አዲስ አበባን ጨምሮ የተለያዩ ትላልቅ ከተሞች አውራጎዳናዎች ከተሽከርካሪ ነፃ ሆነው ህዝቡ በእግሩ እንዲጓዝ  የማድረግ ወርሃዊ መርሃ ግብር ከተጀመረ ሶሰት ወራት ተቆጥረዋል።

በዚህም መሰረት በአዲስ አበባ አራተኛው ወርሃዊ መርሃ ግብር የፊታችን እሁድ የካቲት 24 ቀን 2011 በመዲናው በተመረጡ አምስት ክፍለ ከተሞች ይከናወናል።

የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሳሙኤል ዘመንፈስ ቅዱስ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደተናገሩት በዕለቱ በሚካሄደው የእግር ጉዞ ነዋሪው ለስኳር፣ ደም ግፍት፣ ኩላሊትና ሌሎች ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ትኩረት እንዲሰጥ የሚያግዝ የግንዛቤ መፍጠሪያ ሁነቶችም ይከናወናሉ። 

በአገሪቱ ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች የሚጠቃው የህብረተሰብ ከፍል ከዕለት ወደ ዕለት እየጨመረ መምጣቱን ጠቁመው ህብረተሰቡ በሽታውን በአካል ብቃት እንቅስቃሴና የአመጋጋብ ስርዓትን በመቀየር አስቀድሞ መከላከል ይችላል ብለዋል።

በሽታው በአንድ ቀን የእግር ጉዞ መፍትሄ የሚያገኝ ባይሆንም፤ ከተሽከርካሪ ፍሰት ነጻ በሆኑ መንገደኞች ቀን የሚካሄደው የእግር ጉዞ ነዋሪው ለጤናው ትኩረት እንዲሰጥና  የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ደግሞ ለዚህ አስፈላጊ መሆኑን እንዲረዳ ያግዛል ብለዋል።

በዕለቱ የደም ግፊትና የስኳር ምርመራ፣  የምክር አገልግሎትና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እንደሚካሄድም ጠቁመዋል።

በሶስተኛው የእግር ጉዞ ከሶስት ሺህ ለሚልቁ ዜጎች የደም ግፊትና የስኳር ምርመራ አገልግሎት መሰጠቱን አስታውሰዋል።

በመጪው እሁድ በሚካሄደው ጉዞ በአምስቱም ክፍለ ከተሞች አገልግሎቱን ለመስጠት የቅድመ ዝግጅት ስራ መጠናቀቁን ገልፀዋል። 

የከተማው ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ  የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር  አቶ ታመነ በሌ በበኩላቸው በዕለቱ በአምስት ክፍለ ከተሞች  ስድስት ቦታዎች ለትራፊክ ዝግ ይሆናሉ።

በዚህም መሰረት ከስድስት ኪሎ እስከ  ሚንሊክ አደባባይ፣ ሰሚት አካባቢ ሳፋሪ ትምህርት ቤት እስከ ፊጋ፣ ከልደታ ቤተክርስቲያን እስከ  ብሔራዊ ቲያትር፣  በቤተል ኪዳነ ምህርት ቤተክርስቲያን አካባቢ፣  ሜክስኮ አደባባይ እስከ ልደታ ፍርድ ቤትና  ከጀሞ አንድ እስከ ለቡ መብራት ሃይል ያሉ መንገዶች  ከተሽከርካሪ ነጻ ይሆናሉ።

መንገዶቹ  ከተሽከርካሪ ነጻ የሚሆኑት ከጠዋቱ አስራ ሁለት ሰዓት እስከ ቀኑ 6 ሰዓት  ድረሰ ነው።

አሽከርካሪዎችም በዕለቱ ተለዋጭ መንገድ እንዲጠቀሙ ዳይሬክተሩ አሳስበዋል።

የተጀመረው ስፖርታዊ መርሃ ግብር በህብረተሰቡ ዘንድ በእግር የመጓዝ ባህልን በማዳበር የዜጎችን ጤንነት ለመጠበቅ እንደሚያግዝ ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

መርሃ ግብሩን በመተባበር ያዘጋጁት  ጤና ሚኒስቴር፣ አዲስ አበባ ጤና ቢሮ፣ የከተማው ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲና ትራንስፖርት ባለስልጣን ናቸው።

በዓለም ጤና ድርጅት ሪፖርት መሰረት ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚከሰቱ ሞቶች መካከል የግማሽ ያህሉ ምክንያት ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ናቸው።