በክልሉ ዩኒየኖች የግብርና መካናይዜሽን ቴክኖሎጂን በማስፋፋት አርሶ አደሩን ተጠቃሚ እያደረጉ ነው

64

ጎንደር የካቲት 22/2011 በአማራ ክልል የሚገኙ 11 የገበሬዎች ሕብረት ስራ ዩኒየኖች የግብርና መካናይዜሽን ቴክኖሎጂን በማስፋፋት አርሶ አደሩን የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ማድረግ መጀመራቸውን የክልሉ ሕብረት ሥራ ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ኃይለልኡል ተስፋዬ ሊኢዜአ እንዳስታወቁት ዩኒየኖቹ የግብርናውን ክፍለ ኢኮኖሚ ለማዘመን የሚደረገውን ጥረት በማገዝ ላይ ናቸው፡፡

ዩኒየኖቹ በአሁኑ ወቅት 34 ትራክተሮች፣ 3 የሰብል መሰብሰቢያ ኮምባይነሮችንና 39 የሰብል መውቂያ ማሽኖችን ወደ ክልሉ በማስገባት ለአርሶ አደሩ ድጋፍ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡

የሰብል መሰብሰቢያና መውቂያ ማሽኖቹ የአርሶ አደሩን ጉልበት ከመቆጠብ ባለፈ የምርት ጥራትን በማስጠበቅና ብክነትን በማስቀረት አርሶአደሩን ተጠቃሚ እያደረጉ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

አቶ ኃይለልኡል እንዳሉት ዩኒየኖቹ በምስራቅና ምዕራብ ጎጃም ዞኖች የግብርና መካናይዜሽን ቴክኖሎጂን ማቅረብ የጀመሩ ሲሆን በስራቸው ባሉ 26 መሰረታዊ ማህበራት ለሚገኙ አርሶ አደሮች አገልግሎቱን እየሰጡ መሆናቸውንም አስረድተዋል፡፡

" አርሶ አደሮቹ በተመጣጣኝ ክፍያ በእርሻ ማሳዎቻቸው ላይ ቴክኖሎጂዎቹን እየተጠቀሙ ናቸው " ብለዋል፡፡

የሰብል መሰብሰቢያናመውቂያ ኮምባይነሮቹ ለስንዴ ምርት አሰባሰብ የጎላ እገዛ እያደረጉ ሲሆን የበቆሎ መፈልፈያ ማሽኖችም የአርሶ አደሩና የቤተሰቡን ጉልበት በመቀነስ በኩል አስተዋጽኦ እያደረጉ መሆናቸውን አስረድተዋል።

በምስራቅ ጎጃም ዞን የሚገኘው የጎዛመን ሁለገብ የገበሬዎች ሕብረት ሥራ ዩኒየን ሥራ አስኪያጅ አቶ ጌቱ ባሴ በበኩላቸው እንዳሉት ዩኒየኑ በ10 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ወጪ አንድ የእርሻ ትራክተርና ሁለት ኮምባይነሮችን ገዝቶ ለአርሶአደሩ ድጋፍ እያደረገ ነው፡፡

ዩኒየኑ በ2010/11 የምርት ዘመን 1 ሺህ 500 አርሶ አደሮች ካለሙት የእርሻ ማሳ መሬት 15 ሺህ ኩንታል የስንዴ ምርት በኮምባይነር ሰብስቦ ማስረከቡን ገልጸዋል፡፡

አርሶ አደሮቹ ከዚህ ቀደም ለግለሰብ ኮምባይነር አከራዮች በኩንታል 160 ብር ይከፍሉ እንደነበረ ያስታወሱት አቶ ጌቱ፣ በዩኒየኑ በኩል ለኮምባይነር አገልግሎት በኩንታል 80 ብር እንደሚከፈልና ይህም ከግለሰብ ብዘበዛ አርሶአደሮችን እንደታደጋቸው አስረድተዋል።

"በዚህ ዓመት አንድ የእርሻ ትራክተር ግዢ ፈጽመው ለአርሶአደሩ የእርሻ አገልግሎት ለመስጠት መዘጋጀታቸውን የገለጹት ደግሞ በዚሁ ዞን የሚገኘው የጊዮን ሁለገብ የገበሬዎች ሕብረት ሥራ ዩኒየን ሥራ አስኪያጅ አቶ ቢያዝን መኮንን ናቸው፡፡

በክልሉ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ በሚደረገው መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ሽግግር በክልሉ 20 ዩኒየኖች በዱቄት ማምረት፣ በመኖ፣ በማርና በወተት ማቀናበር እንዲሁም በዘይትና በሳሙና ማምረት ሥራ ላይ ተሰማርተው ይገኛሉ፡፡

በኤክስፖርት ዘርፍ የተሰማሩ የክልሉ ዩኒየኖችም ባለፉት አምስት ዓመታት ለአውሮፓና እስያ ሀገሮች 139ሺህ ኩንታል ሰሊጥ፣ ነጭ ቦለቄ፣ ኑግና ማሾ በመላክ ከ27 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጪ ምንዛሬ ማስገኘታቸው ታውቋል፡፡

በአማራ ክልል 15ሺህ ሕብረት ስራ ማህበራትና 70 ዩኒየኖች ተቋቁመው በመንቀሳቀስ ላይ ሲሆኑ ካፒታላቸውም ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ ደርሷል ፡፡

በክልሉ 3 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር የቁጠባ ገንዘብ ያላቸው 3ሺህ 424 የገንዘብና ቁጠባ ሕብረት ስራ ማህበራት ለአባሎቻቸው የብድር አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸውንም ከኤጀንሲው የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም