በአዲስ አበባ የኦዲት ግኝት ምላሽ ያልሰጡ ተቋማት ላይ እርምጃ ሊወሰድ ነው

105

አዲስ አበባ  የካቲት 21/2011 በአዲስ አበባ የኦዲት ግኝት ምላሽ ያልሰጡ ተቋማት ላይ እርምጃ ሊወሰድ መሆኑን የከተማው ዋና ኦዲተር መሥራያ ቤት ገለጸ። 

የአዲስ አበበ ከተማ አስተዳደር ዋና ኦዲተር በኦዲት ግኝቶችና በሚወሰዱ እርምጃዎች ዙሪያ መግለጫ ሰጥቷል።       

የተቋሙ ዋና ኦዲተር ወይዘሮ ጽጌወይን ካሳ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፤ በመዲናዋ ያሉ ተቋማት ላይ በተለያየ ግዚያት የኦዲት ግኝት ቢኖርም ተገቢው እርምጃ ሲወሰድ አይታይም።  

ለአብነትም ዋና ኦዲተሩ ከ2003 እስከ 2007 ዓ.ም  እንዲሁም ከ2008 እስከ 2010 ዓ.ም ድረስ ኦዲት ተደርገው ምላሽ ያልሰጡ ተቋማትን ለይቶ እንደነበር አስታውሰዋል።   

በዚህ መሰረት ከ2003 እስከ 2007 ዓ.ም 77 ተቋማት ላይ የኦዲት ግኝት መለየቱን ጠቅሰው ከነዚህ መካከል 52 ተቋማት ምላሽ ሲሰጡ፤ 25 የሚሆኑት ደግሞ ምላሽ አልሰጡም ነው ያሉት።   

በተመሳሳይም ከ2008 እስከ 2010 ዓ.ም ወደ 55 የሚጠጉ መስሪያ ቤቶች ምላሽ አለመስጠታቸውን ነው የተናገሩት ወይዘሮ ጽጌወይን። 

ከዚህ በፊት በከተማ አስተዳደሩ የኦዲት ግኝት ተጠያቂነት የሚያሰፍን ሕግ እንዳልነበር ያስታውሱት ዋና ኦዲተሯ በከተማው ምክር ቤት ተጠያቂ የሚያደርግ ሕግ መጽደቁን ተናግረዋል።     

''ምክር ቤቱ ተቋማት ምላሽ እንዲሰጡ የሁለት ወር ግዜ ብቻ ተሰጥቷል'' ያሉት ዋና ኦዲተሯ፤ ከዚሁ ወር መጨረሻ ጀምሮ እርምጃ መውሰድ ይጀመራል ብለዋል።   

እንደ ወይዘሮ ጽጌወይን ገለጻ፤ መስሪያ ቤቶች እስከ የካቲት 24 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ ምላሽ እንዲሰጡ በደብዳቤ እንዲያውቁትም ተደርጓል። 

በግማሽ ዓመቱ የግዥ ሂደት ስርዓትን ሳይጠብቁ የ26 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር ግዥ የፈጸሙ መስሪያ ቤቶች መኖራቸውን ጠቅሰው እነዚህ መስሪያ ቤቶች ምላሽ የመስጠት ግዴታ እንዳአለበቸው አሳስበዋል። 

ከክዋኔ ኦዲት ጋር በተያያዘም በመሬት ልማት ማኔጅመንት ስር ያሉ የመሬት ባንክ አምስት ጽህፈት ቤቶች በሊዝ ተጫርተው ከወሰዱ አልሚዎችና ባለሃብቶች 139 ሚሊዮን ብር ሳይሰበሰቡ ተገኝቷል፤ በዚህ ላይ ክፍለ ከተሞቹ መሰብሰባቸውን ማሳወቅ አለባቸው ሲሉም ተደምጠዋል።

ይህ ካልሆነ ግን እስከ 15 ዓመት ድረስ የሚያስጠይቅ ህግ በቅርቡ በምክር ቤቱ የጸደቀ ሲሆን በዚህ መሰረት እርምጃ እንደሚወስድ ነው የገለጹት።

የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት፣ ውበት መናፈሻና ዘላቂ ማረፊያን ጨምሮ 27 ተቋማት ኦዲት መደረጋቸውን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም