በጋምቤላ የተደራጁ ወጣቶች የገበያ ትስስርና ሥልጠና ጠየቁ

84

ጋምቤላ ጥር 21 / 2011 በጋምቤላ ከተማ ተደራጅተው  በተለያዩ የሥራ ዘርፎች የተሰማሩ ወጣቶች በሥራቸው ውጤታማ ለመሆን የገበያ ትስስርና ሥልጠና እንዲመቻችላቸው ጠየቁ፡፡

የክልሉ የከተሞች የሥራ ዕድል ፈጠራና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ  ለጉዳዮቹ ትኩረት እሰጣለሁ ብሏል፡፡

በከተማዋ በአገልግሎት፣በኮንስትራክሽንና በንግድ ዘርፎች የተሰማሩት ወጣቶች የገበያ ትስስር ስላልተፈጠረላቸውና ሥልጠናዎችን ባለማግኘታቸው ተጠቃሚነታቸው አንስተኛ መሆኑን  ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ገልጸዋል፡፡

ከወጣቶቹ ነፃነት ስንታየሁ እንዳለችው አምስት አባላት ባሉት ማህበር በዳቦ ጋገራ መሰማራታቸውንና ብድር  መውሰዳቸውን ትናገራለች፡፡

ሆኖም የገበያ ትስስር ባለመፈጠሩና የተለያዩ አካላት የሚያደርጉላቸው ድጋፍ በማነሱ የሚፈለገውን ያህል ተጠቃሚ አልሆንም ትላለች፡፡

ሌላው ወጣት ማክ ጆን በበኩሉ  ተደራጅተው በመሥራታቸው ተጠቃሚ እንደሆኑ ይናገራል።ሥልጠና የሚያገኙበት ሁኔታ ቢመቻች ተጠቃሚነታቸው እንደሚያድግ እምነቱን ገልጿል፡፡

የክልሉ የከተሞች የሥራ ዕድል ፈጠራና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ ባደረገላቸው ብድርና ድጋፍ ታግዘው ራሳቸውን ከማስተዳደር አልፈው ለሌሎችም ሥራ መፍጠራቸውን የተናገረው ደግሞ ወጣት ኡቦንግ ኡሞድ ነው፡፡

በብድር 200 ሺህ የሚጠጋ ብር ወስደው የብረታ ብረትና እንጨት ሥራ መጀመራቸውን የገለጸው ወጣቱ፣በአሁኑ ወቅት ካፒታላቸው ከ 500 ሺህ ብር በላይ መድረሱንና ብድር እየመለሱ መሆናቸውንም ተናግሯል፡፡

ይሁን እንጂ በጨረታዎች በመሳተፍ  ተጠቃሚ ልንሆን አልቻልንም በማለት ቅሬታውን አቅርቧል፡፡

የክልሉ የከተሞች የሥራ እድል ፈጠራና ምግብ ዋስትና ኤጀንሲ የገበያ ልማት ዳይሬክተር አቶ ብርሃኑ ዲባባ በሰጡት ምላሽ ወጣቶቹ ያነሷቸው ችግሮች ቢኖሩም፤ የጠባቂነት መንፈስ እንደሚንጸባረቅ ገልጸዋል፡፡

ኢጀንሲው በተለይም ከመስሪያ ቦታ፣በገበያ ትስስርና የጨረታ ተሳትፎ በየደረጃው ከሚገኙ አካላት ጋር በመነጋገር መፍትሄ እንደሚፈለግለት ገልጸዋል።

ኢንተርፕራይዞች ለሁሉም ነገር የመንግሥትን እጅ መጠበቅ እንደማይኖርባቸው ያስረዱት ዳይሬክተሩ፣በተለይም ከሥልጠና ጋር ተያይዘው የሚነሱ ችግሮችን በጋራ ለመፍታት መንቀሳቀስ አለባቸው ብለዋል፡፡

በክልሉ በማምረቻ፣በአገልግሎት፣በኮንስትራክሽን፣በንግድና በከተማ ግብርና የተሰማሩ 3 ሺህ 294 ኢንተርፕራይዞች ከ 21 ሽ 400 በላይ አባላትን አቅፈው በመሥራት ላይ እንደሚገኙ የኤጀንሲው መረጃ ያመለክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም