በሴፍቲኔት ፕሮግራም ከ1 ሚሊዮን የሚበልጡ ዜጎች የቀጥታ ድጋፍ ተጠቃሚ ሆነዋል

2133

አዳማ ግንቦት 21/2010 በገጠርና በከተማ ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም ከ1 ሚሊዮን 157 ሺህ የሚበልጡ ዜጎች የቀጥታ ድጋፍ ተጠቃሚ መሆናቸውን የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሚኒስቴሩ በገጠርና በከተማ ልማታዊ ሴፍቲኔት ከቀጥታ ድጋፍ ተጠቃሚዎች አንጻር የተከናወኑ ተግባራትን በአዳማ ከተማ እየገመገመ ነው።

በሚኒስቴር መስሪያቤቱ የልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ ተስፋዬ ሽፈራው በእዚህ ወቅት እንዳሉት በ2010 በጀት ዓመት የገጠር ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች እየተካሄደ ነው።

በገጠር ድሬዳዋ አስተዳደርን ጨምሮ በአማራ፣ ኦሮሚያ፣ ትግራይ፣ ደቡብ፣ ሐረሪ፣ ሶማሌና አፋር ክልሎች በተመረጡ 349 ወረዳዎች ውስጥ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን በማሳያነት ጠቅሰዋል።

የከተማ ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራምም አዲስ አበባ፣ መቀሌ፣ አዳማና ሃዋሳን ጨምሮ በ11 ከተሞች ተግባራዊ መደረጉን አስረድተዋል።

በገጠርና በከተማ ከ8 ሚሊዮን ለሚበልጡ የፕሮግራሙ ተሳታፊዎች የገንዘብ ክፍያና የምግብ እህል ተደራሽ እየተደረገ መሆኑን አቶ ተስፋዬ ጠቁመዋል።

ከነዚህ ተሳታፊዎች ውስጥ የቀጥታ ድጋፍ ተጠቃሚ ለሆኑት ከ1 ሚሊዮን 157 ሺህ በላይ ዜጎች ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ ከአንድ ቢሊዮን 359 ሚሊዮን ብር በላይ ክፍያ መፈጸሙንም ተናግረዋል።

እንደ አስተባባሪው ገለጻ፣ የቀጥታ ድጋፍ ከተደረገላቸው የሕብረተሰብ ክፍሎች መካከል ሰርተው ለማደር አቅም የሌላቸው አረጋዊያን፣ አካል ጉዳተኞች፣ ጧሪና ደጋፊ የሌላቸውና የአልጋ ቁራኛ የሆኑ ታማሚዎች ይገኙበታል።

በተለይ የልማታዊ ሴፍቲኔት የቀጥታ ድጋፍ ተጠቃሚዎችን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል ከገንዘብ ድጋፍ በተጨማሪ ከመሰረታዊ የማህበራዊ አገልግሎቶች ጋር ለማስተሳሰር እየተሰራ መሆኑን ነው አቶ ተስፋዬ የገለጹት።

መድረኩን የመሩት የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋናው አድማሱ በበኩላቸው በብሔራዊ ማህበራዊ ጥበቃ ፖሊሲው ትኩረት ከተሰጣቸው መካከል በድህነትና በተጋላጭነት ችግር ውስጥ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ይገኙበታል።

“እነዚህ ዜጎች በገጠርና በከተማ ልማታዊ ሴፍቲኔት የቀጥታ ድጋፍ ዘርፍ ያላቸውን ተጠቃሚነት ከተለያዩ ማህበራዊ አገልግሎቶች ጋር በማስተሳሰር የተሻለ ሕይወት እንዲኖራቸው እየተሰራ ነው” ብለዋል።

ይህም የምግብ ዋስትና ያልተረጋገጠላቸው የገጠርና የከተማ ቤተሰቦች ካሉባቸው ችግሮች በፍጥነት እንዲያገግሙ፣ ኑሯቸው እንዲሻሻልና የምግብ ዋስትናቸውን ለማረጋገጥ እንደሚያስችል አስረድተዋል።

የመድረኩ ዓላማም የፕሮግራሙን የአፈጻጸም ሂደት ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመገምገም በትግበራ ሂደት ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን በመፍታት በቀጣይ የሚሰጡ አገልግሎቶ ፍትሃዊ፣ ተደራሽና ቀልጣፋ እንዲሆን ለማድረግ መሆኑን አስረድተዋል።

ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል በኦሮሚያ ክልል ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ የማህበራዊ ደህንነት ዳይሬክተር አቶ መርጋ ምትኬ በሰጡት አስተያየት ” ፕሮግራሙ በክልሉ በተመረጡ 90 ወረዳዎችና በአዳማ ከተማ ተግባራዊ ሆኗል ” ብለዋል።

እስካሁንም በፕሮግራሙ አቅመ ደካማና ችግረኛ ለሆኑ 228 ሺህ ዜጎች የቀጥታ ፋይናንስ ድጋፍና ማህበራዊ አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።

ድጋፉ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ የሕብረተሰብ ክፍሎች በአግባቡ እየደረሰ ስለመሆኑ ተገቢ ክትትል እንደሚደረግም አመልክተዋል።

ለሁለት ቀናት እየተካሄደ ባለው መድረክ ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም ከተጀመረባቸው ክልሎችና ከተሞች የተውጣጡ አስፈጻሚ አካላት በመሳተፍ ላይ መሆናቸውን ተዘግቧል።