መገናኛ ብዙሀን የቻይና-አፍሪካ ግንኙነትን ይበልጥ ለማጠናከር እንደ ድልድይ ያገለግላሉ

939

ቤጂንግ – ቻይና የካቲት 20/2011  መገናኛ ብዙሀን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ የመጣውን የቻይና እና የአፍሪካ ሀገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ይበልጥ እንዲጎለብት ሁለቱን ስትራቴጂያዊ አጋሮችን የሚያቀራርቡ ስራዎችን በመስራት ድልድይ መሆን እንዳለባቸው የቻይና ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ምክትል ፕሬዝዳንት ተናገሩ፡፡

የቻይና ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ማህበር ም/ፕሬዝዳንት ሁ ጀንግዩ ይህን ያሉት ሀገሪቱ ለአፍሪካውያን ጋዜጠኞች በየአመቱ የምትሰጠውን የቻይና አፍሪካ ፕሬስ ሴንተር የስልጠና መርሀ ግብር በከፈቱበት ወቅት ነው፡፡

የቻይና ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ማህበር በዲፕሎማቶች መኖሪያ ቅጥር ግቢ ዛሬ ባዘጋጀው ፕሮግራም ላይ ንግግር ያደረጉት ም/ፕሬዝዳንቱ፤ ከጥንት ጀምሮ ቻይናውያን እና አፍሪካውያን የምረዳዱ ወንድማማቾች እና አጋሮች ብሎም እጣ ፋንታቸውን  የምጋሩ ማህበረሰቦች ናቸው ብለዋል፡፡

መገናኛ ብዙሀን ይህን ለዘመናት የቆየውን ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የጋራ ትብብሮችን ማጉላት፣ ህዝቦችን ማቀራረብ፣ ሰላምን መስበክ እና ቻይናንም በማስተዋወቅ እውነት ላይ የተመሰረቱ ዘገባዎቻቸውን እንዲያሰራጩ ነው የጠቆሙት፡፡

እኤአ 2019 የቻይና መንግስት”ያመቻቸላችሁን ስልጠና የምትከታተሉ ጋዜጠኞች በሚኖራችሁ ቆይታ በያዛችሁት እስክሪብቶ እና ካሜራ ያያችሁትን፤ የሰማችሁትን መልዕክት ለአህጉራችሁ እና ለአለም ማህበረሰብ ለማድረስ እንደ ድልድይ የምታገለግሉ ናችሁ”ሲሉም ተናግረዋል፡፡


ጋዜጠኛ ሙባራክ ሙጋቦ

አፍሪካውያን ጋዜጠኞችን በመወከል ንግግር ያደረገው ጋዜጠኛ ሙባራክ ሙጋቦ፤ የቻይና መንግስት ለአፍሪካውያን ጋዜጠኞች የሰጠውን የስልጠና እድል በማድነቅ ቻይና በአፍሪካ ግንባር ቀደም ሚና በመጫወት ላይ ትገኛለች ብሏል፡፡

ጋዜጠኛ ሙባራክ እንደገለጸው ቻይና በአፍሪካ አህጉር የዘረጋቻቸው በርካታ ፕሮጀክቶች እና የኢንቨስትመንት ስራዎች እንደ አጠቃላይ አፍሪካውያን ዜጎችን የሚጠቅሙ እና የሀገራት የኢኮኖሚ እድገትን የሚያፋጥኑ ናቸው፡፡

የቻያና ኩባንያዎች እንደ ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ዩጋንጋ፣ አልጄሪያ እና አንጎላ በመሳሰሉ ሀገራት የገነቧቸው የኢንዱስትሪ ፓርኮች፣ የመሰረተ ልማት ስራዎች እና ሌሎች የትብብር ስራዎች እንደ ማሳያ ቀርበዋል፡፡

በዚህም ቻይናውያን ኩባንያዎች እና መንግስታቸው በፈጠሩት የስራ እድል ወጣት አፍሪካውያን ተጠቃሚ ሆነዋል፤ ከቻይናውያን ባለሙያዎች የሚያገኙት የእውቀት እና ክህሎች ሽግግግርም እየተሻሻለ መጥቷል ብለዋል፡፡

ጋዜጠኛ ሙባራክ ይህን ጠንካራ የጋራ ትብብር በተዛባ መንገድ የሚዘግቡትን ወደ ጎን በመተው፤ ስለ ቻይና የተመለከትነውን እውነተኛ ዘገባ ለህዝባችን ማሳወቅና ማስተማር ይኖርብናል ነው ያለው፡፡

በሌላ በኩል ይህ ስልጠና የቻይና እና አፍሪካ ሀገራት የሚዲያ ተቋማት ልምድ እንዲለዋወጡ እና በትብብር እንዲሰሩ እድል እንደሚፈጥረላቸው ም/ፕሬዝዳንት ሁ ጀንግዩ ተናግረዋል፡፡

በስልጠና መርሀ ግብሩ የመክፈቻ ስነስርዓት ላይ የኢትዮጵያን ኤምባሲን ጨምሮ የሌሎች የውጭ ሀገራት ኤምባሲ ተወካዮች ተገኝተዋል።

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር 2012 የተጀመረው የቻይና- አፍሪካ ፕሬስ ሴንተር የስልጠና ፕሮግራም ዘንድሮም ለቀጣዮቹ አስር ወራት የሚቆይ ይሆናል፡፡

ከተለያዩ የአህጉሪቱ ሀገራት የተውጣጡ 34 ጋዜጠኞች ስልጠናውን ይታደማሉ፡፡