ኢትዮጵያዊያን ሀገራዊ ፍቅራቸውን በተግባር ሊገልጹ ይገባል--- የብሄራዊ እርቀ ሰላም

ደሴ  የካቲት 20/2011 ኢትዮጵያዊያን የየአካባቢያቸውን  ሰላም በመጠበቅ  ሀገራዊ ፍቅራቸውና መውደዳቸውን  በተግባር ሊገልጹ እንደሚገባ  የብሄራዊ እርቀ ሰላም ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አሳሰቡ፡፡ 

" ሀገራዊ የሰላም ፣ ዴሞክራሲና የልማት ኮንፈረንስ ለኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ሽግግር" በሚል መሪ ሀሳብ የተዘጋጀ  ውይይት  በወሎ ዩኒቨርሲቲ እየተካሄደ ነው፡፡

በዚህ ወቅት ምክትል ኮምሽነር ወይዘሮ የትነበርሽ ንጉሴ እንዳሉት ሁሉም ዜጋ የአካባቢውን ሰላም ነቅቶ በመጠበቅ ሀገራዊ ፍቅሩን በተግባር ሊገልጽ ይገባል፡፡

ለዴሞክራሲው መጎልበትና የህግ የበላይነት መከበር የህብረተሰቡ ድርሻ የጎላ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

" የአባቶቻችን አንድነትና የመቻቻል እሴት ከታሪክ በመገንዘብ ኢትዮጵያን ከጥፋት በመታደግ አገራዊ ግዴታችን መወጣት አማራጭ የሌለዉ መፍትሄ ነው " ብለዋል፡፡

ልማትና ዴሞክራሲ ጎልብቶ ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍልና የህግ የበላይነት እንዲሰፍን በቅድሚያ ውስጣዊ ሰላም ማስከበር ያስፈልጋል፡፡

" ህብረተሰቡ ከእልህና ስሜት ተላቆ በሚለያዩን ጉዳዮች ሳይሆን አንድ በሚያደርጉን ጉዳዮች ላይ ሊያተኩር ይገባል " ያሉት ምክትል ኮሚሽነሯ አቋም ይዞ በድፍረት ለኢትዮጵያ አንድነትና ሰላም እንዲሰራም ጠይቀዋል፡፡

የአማራ ክልል  ርዕሰ መስተዳደር ጽህፈት ቤት የበየነ መንግስታት ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ዮሐንስ ቧያለዉ በበኩላቸው "አባቶቻችን ለሰላም ሲሉ ተቻችለውና ተከባብረው አንድነታችን በማስጠበቅ የኢትዮጵያን ዳር ድንበር አስከብረዋል" ብለዋል፡፡

ትውልዱም ይህንን አኩሪ ታሪኩን ጠብቆ አገሩን ከድህነት ለማውጣት  የደርሻውን እንዲወጣ መልዕክታቸወን አስተላልፈዋል፡፡

" አዲሱ ትውልድ አባቶችና ሽማግሌዎች ያሉትና ባለመቀበሉና ባለማክበሩ ወደ እርስ በእስር ግጭትና ጥፋት እያመራን ነው" ያሉት ደግሞ የታሪክ ተመራማሪው  አቶ ኢብራሂም ሙሉሽዋ ናቸው፡፡

ለዚህ ደግሞ ከታች እስከ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ላሉ ተማሪዎች ትክክለኛውን ታሪክ ጊዜ ተወስዶ ማስተማር እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡

" ዩንቨርሲቲው  ትክክለኛውን ታሪክ ለትውልዱ በማውረስ ለአንድነትና ሰላም መረጋገጥ የድርሻውን ይወጣል" ያሉት ደግሞ የወሎ ዩንቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር አባተ ጌታሁን ናቸው፡፡

ለዚህ ደግሞ ወሎ የመቻቻልና የአብሮነት ባህሉን አዳብሮ አማራውን ከኦሮሞ፣ ከአፋር፣ ከትግራይና ከሌሎችም ኢትዮጵያወቂያን  ጋር ለማስተሳሰር እንደ ድልድይ  እንደሚያገለግል አመልክተዋል፡፡

በውይይቱ የተለያዩ የኢትዮጵያን ታሪኮች የሚያስቃኙና ለወቅታዊ ሀገራዊ ችግሮች መፍትሄ አመላካች የሆኑ ጥናታዊ ጽሁፎችም እየቀረቡ ይገኛል፡፡

ለሁለት ቀናት በሚቆየው በዚሁ ውይይት ከተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የተወጣጡ የመንግስት አመራሮችና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምሁራን እየተሳተፉ መሆናቸውን ሪፖርተራችን ከስፍራው ዘግቧል፡፡

---END---

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም