በሀዋሳ የንግዱን ማህበረሰብ ከኢንደስትሪያል ፓርኩ ጋር ግንኙነታቸውን ማጠናከር እንደሚገባ ተመለከተ

615

ሀዋሳ የካቲት 20/2011 የሀዋሳ ከተማና አካባቢው የንግድ ማህበረሰብ ከሀዋሳ ኢንደስትሪያል ፓርክ ጋር  ግንኙነታቸውን ማጠናከር እንደሚገባ ተመለከተ፡፡

በኢንዱስትሪያል ፓርኩና በቱሪዝም ሴክተር የኢንተርፕሪነር ስርዓተ ምህዳር ለማጠናከር በሚል የተዘጋጀ የምክክር መድረክ በሀዋሳ  ተካሄዷል፡፡

በመድረኩ በቀረበ ጥናታዊ ጽሁፍና ውይይት ወቅት   የሀዋሳ ከተማን የንግድ ማህበረሰብ በማሳተፍ  ተጠቃሚ ለማድረግ የኢንደስትሪያል ፓርኩ በትኩረት እንዲሰራ ተጠይቋል፡፡

በሀዋሳ ከተማ በጽህፈትና ጽዳት ዕቃዎች አቅራቢነት የተሰማሩት አቶ ጎበና በሪ  እንዳሉት ከኢንደስትሪያል ፓርኩ ጋር በቅርበት እየሰሩ ቢሆንም  አብዛኛውን ጊዜ ግዥ የሚፈጸመው ከሌላ አካባቢና በግልጽ ጨረታ ባለመሆኑ ተጠቃሚ አይደሉም፡፡

” በኢንደስትሪል ፓርኩ የተሰማሩ ባለሀብቶች የሚያስፈልጋቸውን ነገር የምናውቅበት መንገድ ባለመኖሩ እየተቸገርን ነው “ብለዋል።

የንግድ ማህበረሰብ የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች ለፓርኩ ማቅረብ እንዲችል ከማድረግ አንጻር ክፍተቶች እንዳሉ ተወስቷል፡፡

የሀዋሳ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ሚልኪያስ ማንዴቦ  በበኩላቸው የጥናቱ ዓላማ የሀዋሳ ከተማን የንግድን ማህበረሰብ በኢንደስትሪያል ፓርኩ የተፈጠረለትን ዕድል መጠቀም የሚችልበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ታስቦ ነው።

ፓርኩ ከፈጠረው የስራ እድልና ለሀገር ከፍተኛ የውጪ ምንዛሪ ከማስገኘት ባለፈ ለአካባቢው የንግድ ስራ መቀላጠፍ  ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸዋል።

ይህን ዕድል መጠቀም የሚቻልበትን ሁኔታ ለመለየት ጥናት መደረጉን ገልጸው ከጥናቱ አንጻር በፓርኩና በንግድ ማህበረሰቡ መካከል ያለው ግንኙነት የላላ በመሆኑ መጠናከር እንደሚገባው አመልክተዋል፡፡

” በጥናቱ ያሉትን ክፍተቶች ማየት የቻልንበትና ትልቅ የመረጃ ምንጭ አድርገን እንወስደዋለን” ያሉት ደግሞ የሀዋሳ ኢንደስትሪያል ፓርክ ስራ አስኪያጅ አቶ ፍጹም ከተማ ናቸው፡፡ 

የሀዋሳ ከተማ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ከተባባሪው ጋር ባዘጋጀው የምክክር መድረኩ  ከሀዋሳ ከተማ የንግድ ማህበረሰብ ፣ ከፋይናንስ ተቋማትና  ከሌሎችም ክፍሎች የተወጣጡ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።