የይስማ ንጉስ ሙዚየም እስኪጠናቀቅ ድረስ ድጋፋችንን አጠናክረን እንቀጥላለን...የአምባሰል ወረዳ ነዋሪዎች

82

ደሴ የካቲት 20/2011 ደቡብ ወሎ ወሎ ዞን አምባሰል ወረዳ ግንባታው የተጀመረው "ይስማ ንጉስ ሙዚየም" እስኪጠናቀቅ ድረስ ድጋፋችንን አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉ የአምባሰል ወረዳ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡

የደቡብ ወሎ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ በበኩሉ ሙዚየሙ በታቀደለት የጊዜ ገደብ ውስጥ እንዲጠናቀቅ ክትትልና ድጋፍ እያደረገ መሆኑን አስታውቋል፡፡

በአምባሰል ወረዳ የቀበሌ 3 ነዋሪ አቶ ጉማታው ያሲን ለኢዜአ እንደገለጹት በ1881 ዓ.ም አፄ ሚኒሊክ ከጣሊያን ጋር የውጫሌውን ስምምነት የተፈራረሙበት ታሪካዊ ቦታ ትኩረት ተነፍጎት መቆየቱ የአካባቢውን ነዋሪ ቅር አሰኝቶ ቆይቷል፡፡

በቦታው ላይ ሙዚየም ተሰርቶ ታሪኩ ለትውልድ እንዲተላለፍ ህብረተሰቡ በተደጋጋሚ ያነሳው ጥያቄ ምላሽ አግኝቶ የሙዚየሙ ግንባታ ሥራ  በመጀመሩም መደሰታቸውን ገልጸዋል።

ሙዚየሙ በተያዘለት የጊዜ ገደብ ውስጥ ተገንብቶ እንዲጠናቀቅም የጀመሩትን ድጋፍ እንደሚያጠናክሩ ተናግረዋል፡፡

"ታሪክ እንዳይጠፋ በሚል ሩብ ሄክታር መሬቴን ያለ ካሳ በሙዚየሙ እንዲካለል አድርጊያለሁ" ያሉት አቶ ጉማታው፣ ከእዚህ በተጨማሪ  ለትራንስፖርት አስቸጋሪ በሆኑ ቦታዎች የግንባታ ቁሳቁሶችን በማመላለስ ድጋፍ እያደረጉ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

የሙዚየሙ ግንባታ እስኪጠናቀቅ ድረስም ህብረተሰቡን በማስተባበር አሸዋ፣ ሲሚንቶ፣ ድንጋይና ሌሎችንም አስፈላጊ የግንባታ ግብአቶች በማቅረብና በመንከባከብ የድርሻቸውን እንደሚወጡ አረጋግጠዋል፡፡

ሌላው አርሶ አደር ታደሰ መኮንን በበኩላቸው "የሁሉም ኢትዮጵያውን የጋራ ድል መነሻ የሆነው ታሪካዊ ሥፍራ ለከብቶች የግጦሽ ቦታ ሆኖ ቀይቷል" ብለዋል፡፡

የዘመናት ጥያቄያቸው ምላሽ አግኝቶ የሙዚየሙ ግንባታ መጀመሩ እንዳስደሰታቸው ጠቁመው ለሙዚየሙ ግንባታ የሚያስፈልገውን ድጋፍ እያደረጉ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡

አርሶ አደሩ አንዳሉት የአካባቢው ሕብረተሰብ ተስፋ ሳይቆርጥ በየዓመቱ የሚከበረውን የአድዋ ድል በዓል ሙዚየሙ በሚገነባበት ቦታ ላይ ሆኖ ታሪኩን እያስታወሰና እየዘከር ሲያከብረው ቆይቷል፡፡

ሙዚየሙ በሚገነባበት አካባቢ በክረምት መኪና ስለማይገባ ወጣቱን በማነሳሳት የግንባታ እቃዎችን በሰው ጉልበት እንዲደርሱ ማድረጋቸውንና ይህንን ድጋፋቸውን እንደሚያጠናክሩ ተናግረዋል፡፡

መንግስት ሙዚየሙ ተገንብቶ ብቻ እንዳይቀር የአካባቢውን ባህል የሚገልጹ ቁሳቁሶችን በማሟላት፣ መንገዱን በማስተካከልና አካባቢውን በማልማት ለቱሪስቶች ምቹ እንዲያደርግም ጠይቀዋል፡፡

የደቡብ ወሎ ዞን ባህል ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ አቶ ሱሌይማን እሸቱ በበኩላቸው በህብረተሰቡ ከፍተኛ ግፊት ግንባታው የተጀመረው ይስማ ንጉስ ሙዚየም በታቀደለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ ተገቢ ክትትልና ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

"የጀግኖች አባቶች ታሪክና አንድነት ለትውልዱ ለማስተላለፍ በአምባሰል ወረዳ የውጫሌ ስምምነት በተፈረመበት ቦታ መንግስት 25 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር መድቦ ታሪኩን በሚገልጽ ሁኔታ ሙዚየሙን እያስገነባ ነው" ብለዋል፡፡

በጀት በሚፈለገው ወቅት እንዲለቀቅና አስፈላጊ የግንባታ እቃዎችም እንዲገቡ በማድረግ በህብረተሰቡ ድጋፍ እንዲፋጠን እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ህብረተሰቡ በግንባታው ተደስቶ ለጉልበቱና ለጊዜው ሳይሳሳ ድጋፍ ከማድረጉም ባለፈ ለጎብኚዎች ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠር ከ4 ሄክታር መሬት በላይ ለሙዚዬም ግንባታ በስጦታ ማበርከቱን አስረድተዋል፡፡

በ2010 ዓ.ም የካቲት ወር ላይ ግንባታው የተጀመረው ሙዚየም በሁለት ዓመት ውስጥ የሚጠናቀቀ ሲሆን አስፈላጊ ታሪካዊ ቅርሶችን በሙዚየሙ ለእይታ ለማቅረብ ከወዲሁ እየተሰራ መሆኑንም አመልክተዋል።

የሙዚየሙን ግንባታ ሥራ እያከናወነ ያለው የአማራ ህንጻ ሥራዎች ተቋራጭ ሲሆን የፕሮጀክቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ ዮሐንስ አሰፋ ግንባታውን ለማፋጠን ትኩረት ሰጥተው እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ግንባታው 44 በመቶ የደረሰ ሲሆን እስካሁንም አስቸጋሪና ከባድ የተባሉ ሥራዎች በመከናወናቸው ሙዚየሙን ከታቀደው ጊዜ ቀድመው በማጠናቀቅ ለማስረከብ በትኩረት እየሰሩ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

ሙዚየሙ 3 ህንጻዎች ያሉት ሲሆን አንዱ ባለ አንድ ፎቅ መሆኑንና አሰራሩም ታሪኩን በሚገልጽ መልኩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የህብረተሰቡ በጉልበት ከፍተኛ እገዛ እያደረጉላቸው መሆኑን ጠቅሰው እስካሁንም በግንባታው ለ60 ወጣቶች የስራ እድል መፈጠሩን ተናግረዋል፡፡

የስራ እድል ከተፈጠረለቸዉ ወጣቶች መካከል ወጣት መሃመድ ወርቁ 10ኛ ክፍል አጠናቆ ለሁለት ዓመታት ከቤተሰብ ጋር በጥገኝነት መቆየቱን አስታዉሷል፡፡

አሁን በተፈጠረለት የስራ እድል በወር ሁለት ሺህ 500 ብር እያገኘ መስራቱንና የግንባታ ሙያ መልመዱን ተናግሯል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም