27ኛው የግንቦት 20 የድል በዓል በተለያዩ አገሮች ተከበረ

64
አዲስ አበባ ግንቦት 21/2010 27ኛው የግንቦት 20 ክብረ በዓል በደቡብ አፍሪካ፣ በጃፓን፣ በሱዳንና ደቡብ ሱዳን የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላትና የየአገሮቹ ተወካዮች በተገኙበት ተከበረ። በዓሉ በየአገሮቹ በሚገኙ የኢትዮጵያ አምባሳደሮችና የማኅበረሰብ አባላት በተገኙበት በቶኪዮ፣ በፕሪቶሪያ፣ በካርቱምና በጁባ በድምቀት ተከብሯል። የጃፓንን መንግስት ወክለው የተገኙት የአገሪቱ የካቢኔ ጉዳዮች ምክትል ሹም የሱቶሹ ኒሲሙራ ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የመልካም ምኞት መግለጫ አቅርበው፤ አገራቸው በሁለትዮሽ የንግድና የህዝብ ለህዝብ መድረኮች፣ የአፍሪካ ጃፓን ፎረም የምታደርጋቸውን ትብብር አጠናክራ እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል። የደቡብ አፍሪካ ፐብሊክ ስራዎች ሚኒስቴር ዳይሬክተር ጀኔራል ሳም ቩኮሌ የኢትዮጵያን ፈጣን ኢኮኖሚያዊ ዕድገትና በቅርቡ የተወሰዱ የሪፎርም ስራዎችን አድንቀዋል። በጃፓን የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ቻም ኡጋላ እና በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ዶክተር ሽፈራው ተክለማርያም ግንቦት 20 ኢትዮጵያ ከአምባገነን ስርዓት ወደ አዲስ ዴሞክራሲያዊ ህገ መንግስታዊ ስርዓት የተሸጋገረችበት ቀን መሆኑን ተናግረዋል። በደቡብ ሱዳን የኢፌዴሪ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ፍስሃ ሻውል ኢትዮጵያ ለደቡብ ሱዳን ነፃነት ከፍተኛ ድጋፍ እንዳደረገችና በአገሪቱ ሰላምና መረጋጋት እንዲመጣ እየሰራች መሆኑን ገልጸዋል። በሱዳን ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ሙሉጌታ ዘውዴ ባደረጉት ንግግር ባለፉት 27 ዓመታት በድህነት ላይ በተደረገ ዘመቻ በግብርና በከተማ ልማት፣ በትምህርት፣ በጤና እና በሌሎች የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎች አበረታች ለውጦች መመዝገባቸውን ገልጸዋል። በቅርቡ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጥያቄ መሰረት በአገሪቱ ውስጥ የነበሩ ኢትዮጵያውያን እስረኞች መፈታታቸውም የአገሮቹን ወዳጅነት ወደላቀ ደረጃ መሸጋገሩን የሚያመላክት እንደሆነ መጠቆማቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለኢዜአ የላከው መግለጫ ያመለክታል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም