በጉጂ ዞን ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ላይ ለመንግስት ሠራተኞች ነጻ ምርመራ እየተሰጠ ነው

670

ነገሌ የካቲት 20 / 2011 በጉጂ ዞን ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች በህብረተሰቡ ላይ የሚያደርሱትን የጤና ጉዳት አስቀድሞ ለመከላከል ለመንግስት ሠራተኞች ነጻ የምርመራ አገልግሎት እየተሰጠ ነው።     

በዞኑ ጤና ጥበቃ ጽህፈት ቤት ተላላፊና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች መከላከል ባለሙያ አቶ ታከለ ኡቱራ እንዳስታወቁት ነጻ የምርመራ አገልግሎቱ  እየተሰጠ ያለው ከየካቲት 18 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ ለአምስት ተከታታይ ቀናት ነው።

ምርመራውም ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች የተያዙ ሰዎችን ለይቶ ተገቢውን ሕክምና እንዲጀምሩ ለማድረግ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸዋል።

አቶ ታከለ እንዳሉት ምርመራው ያተኮረው በካንሰር፣ በስኳር፣ በደም ግፊት፣ በሳንባ ነቀርሳና በልብ በሽታዎች ላይ ነው።

ቀደም ብሎ በየደረጃው በሚገኙ የጤና ተቋማት በተካሄደው ጥናት እነዚህ በሽታዎች በህብረተሰቡ ላይ በስፋት እየተከሰቱ መምጣታቸውን  መረጋገጡንም አመልክተዋል።

በሽታዎቹ በጤና ላይ የከፋ ጉዳት ከማድረሳቸው በፊት አስቀድሞ ለመከላከል ነጻ ምርመራ መዘጋጀቱንና በእዚህም 800 የመንግስት ሠራተኞች ተጠቃሚ ይሆናሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ አስረድተዋል፡፡

እንደ አቶ ታከለ ገለጻ በነገሌ ከተማ ባለፉት ሁለት ቀናት ምርመራ ካካሄዱት 130 ሰዎች ውስጥ አስሩ የስኳርና የደም ግፊት የጤና ችግር ተገኝቶባቸው የሕክምና ክተትል እንዲያደርጉ ተደርጓል።

በቀጣይም ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች በሕብረተሰቡ ላይ የሚያስከትሉትን ጉዳት አስቀድሞ ለመከላከል የዞኑን ህዝብ ግንዛቤ የማሳደግ ሥራ በዞኑ በሚገኙ ወረዳዎች በተመሳሳይ እንደሚከናወን ተናግረዋል።

የነጻ ሕክምና ምርመራው ተጠቃሚ ከሆኑ ሠራተኞች መካከል የነገሌ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ጌጤነሽ ኃይሉ የምርመራ አገልግሎቱ በቀጣይ የአመጋገብ ልምዳቸውን በማስተካከል ራሳቸውን ተላላፊ ካልሆኑ በሽታዎች ለመጠበቅ እንደሚረዳቸው ገልጸዋል።

በምርመራ ውጤቱ መሰረት የሰውነታቸውን ክብደት ለመቀነስ ስፖርት እንዲሰሩና በየጊዜው የጤና ምርመራ እንዲያደርጉ በጤና ባለሙያዎች ምክር ማግኘታቸውንም ተናግረዋል።

ለመጀመሪያ ጊዜ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለማወቅ ምርመራ ማድረጉን የገለጸው ወጣት አማኑኤል ገብረማሪያም በበኩሉ የምርመራው ውጤት ለጤና ጎጂ ከሆነው የአልኮል መጠጥ እንዲቆጠብ ማሳየቱን ተናግሯል።

” የቅድመ ምርመራ ልምድና ባህላችን ደካማ ነው ” ያለው ወጣቱ፣ ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች በቀላሉ እየተጋለጠ ያለውን ህብረተሰብ ለመታደግ ነጻ ምርመራው አስፈላጊና ወሳኝ በመሆኑ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቋል።