የአማራና ቅማንት ህዝቦችን ለማቀራረብ እንደሚሰሩ የሀገር ሽማግሌዎች ገለጹ

137

ጎንደር የካቲት 20/2011 የአማራና ቅማንት ህዝቦችን በማቀራረብ የአካባቢውን ሰላም ለመመለስ እንደሚሰሩ በማዕከላዊ ጎንደር ላይ አርማጭሆና የታች አርማጭሆ ወረዳዎች የጋራ የሰላም ሀገር ሽማግሌዎች ገለፁ፡፡

የሰላም ሀገር ሽማግሌዎቹ  በትክል ድንጋይ ከተማ የጋራ ሰላም ውይይት አካሂደዋል፡፡

የላይ አርማጭሆ ወረዳ ነዋሪው የሀገር ሽማግሌ  አቶ አየነው መለሰ እንደተናገሩት ከሁለቱ ወረዳዎች የተወጣጣው የጋራ የሰላም የሀገር ሽማግሌዎች ቡድን መደራጀቱ በአካባቢያቸው የከፋ ግጭት እንዳይይፈጠር አግዟል፡፡

ለግጭት መንስኤ የሚሆኑ ልዩነቶችን በማጥበብ የሁለቱን ህዝቦች ሰላም በማድፍረስ ያልተገባ ጥቅም የሚፈልጉ ግለሰቦችን ስርዓት ለማስያዝ የጋራ ጥረት እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡

" ያለፈውን ቂምና በቀል በመተው ነባሩን ፍቅራችን መመለስና ለሰላም ዘብ መቆም ይኖርብናል" ያሉት አቶ አየነው ይህንን ኃላፊነታቸውንም እንደሚወጡ አመላክተዋል፡፡

ከታች አርማጭሆ ወረዳ የመጡት አቶ አንዳርጋቸው ሙጨ በበኩላቸው የአማራና ቅማንት ህዝቦች  ተቀራርበው ፍቅርና አንድነታቸው እንዲጠናከር እንደሚሰሩ ገልጸዋል፡፡

ለሀገር ሽማግሌዎች እንቅፋት የሚሆኑ አንዳንድ ግለሰቦችና አመለካከቶች እንደሚኖሩ በማሰብም ተስፋ ሳይቆርጡ መስራታቸውን እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል፡፡

" የጋራ የሰላም ሽማግሌዎቹ የተጀመረውን የሰላም ውይይት ውጤት እንዲያመጣ  በሌሎች አካባቢዎችም ተንቀሳቅሰው ተመሳሳይ ሰላም ወዳድ ሽማግሌዎችን በመምረጥ ሁለቱን ህዝብ ወደ ቀደመ አንድነቱ እንመልሳለን "ብለዋል፡፡

በውይይቱ የተገኙትና በአሜሪካ የሚኖሩት የአካባቢው ተወላጅ ዲያቆን አማኑኤል አወቀ የሀገር ሽማግሌዎቹን በገንዘብና በሃሳብ ለመደገፍ ቃል ገብተዋል፡፡ ፡

በውጭ የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያንን በማስተባበር የሀገር ሽማግሌዎች ጥረት እንደሚደግፉ ሌላው  በአሜሪካ የሚኖሩት አቶ ሙሉጌታ ንጉሴ በሰጡት አስተያየት አረጋግጠዋል፡፡

ከሁለቱም ህዝቦች ያልተገባ ጥቅም ፈላጊዎችን በማጋለጥ ወደ ህግ እንዲቀርቡ ማድረግ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

ሌላው የውይይቱ ተሳታፊ አቶ ባዜ ዘርይሁን " በሁለቱ ህዝቦች መካከል ግጭት እንዲፈጠር የሚያደርጉ አመራሮችም በህግ አግባብ መጠየቅ ይገባቸዋል "ብለዋል ፡፡

የሰላም የሀገር ሽማግሌዎቹ ጥረትን በመደገፍ አሁን የተፈጠረው አንፃራዊ ሰላም ዘላቂ እንዲሆን  የበኩላቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል፡፡

በአካባቢው የሀገር መከላከያ ሰራዊት አዛዥ ኮረኔል ገብረመስቀል ገብረስላሴ "የሀገር ሽማግሌዎቹን ጥረት በመደገፍ ሰራዊቱ ለሰላም መከበር በጋራ ይሰራል" ብለዋል፡፡

" በሁለቱ ህዝቦች መካከል ፍፁም ፍቅር እንዳለ በአይኔ ተመልክቻለሁ" ያሉት ኮረኔሉ በግጭቱ ተጠቃሚ ለመሆን የሚፈልጉ ግለሰቦችን በጋራ መታገል እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡

የጋራ የሰላም ሽማግሌዎቹ የካቲት 21/2011ዓ.ም. ከሰባት ወረዳዎች የተወጣጡ የሀገር ሽማግሌዎችን በመምረጥ ታች አርማጭሆ በሳንጃ ከተማ  በጋራ ለመወያየት ቀጠሮ ይዘዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም