ለከፍተኛ ትምህርት ጥራት መረጋገጥ የኖርዌይ ድጋፍ ጉልህ ሚና አለው -የመቀሌና ሃዋሳ ዩኒቨርሲቲዎች

67

መቀሌ የካቲት 20/6/2011 ኖርዌይ ለኢትዮጵያ የከፍተኛ ትምህርት ጥራትና ስኬታማነት የምታደርገው እገዛ አበረታች ውጤት የሚታይበት መሆኑን የመቀሌና የሃዋሳ ዩኒቨርሲቲዎች አስታወቁ።

ለሃዋሳና መቀሌ ዩኒቨርሲቲዎች የኖርዌይ መንግስት ድጋፍ ማድረግ የጀመረበትን 25ኛ ዓመት በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ አክብሯል።

በዚሁ ወቅት የመቐለ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ክንደያ ገብረሕይወት እንደተናገሩት ዩኒቨርሲቲው አሁን ለደረሰበት ደረጃ እንዲበቃ የኖርዌይ መንግስት በስርዓተ-ትምህርት ቀረፃ፤በመምህራን አቅም ግንባታና በሌሎች ድጋፎች ያበረከተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው።

ዩኒቨርሲቲው በአሁኑ ሰዓት ካሉት 200 የዶክትሬት ዲግሪ መምህራን መካከል 90 ከመቶ የሚሆኑትና በርካታዎቹ የሁለተኛ ዲግሪ መምህራን በኖርዌይ መንግስት ድጋፍ የተማሩ መሆናቸውንም ፕሮፌሰሩ አስታወቀዋል።

“የኖርዌይ መንግስት ለ25 ዓመታት ባደረገው ያልተቋረጠ ድጋፍም ዩኒቨርሲቲው በ164 የትምህርት ፕሮግራሞች የዶክትሬትና የማስተርስ ዲግሬ የትምህርት መርሃ-ግብር ስልጠናዎችን እንዲሰጥ አስችሎታል” ብለዋል።

በዩኒቨርሲቲው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ትብብር ኃላፊ ዶክተር ደስታ በርሀ በበኩላቸው ለ25 ዓመታት የኖርዌይ መንግስት ከዩኒቨርሲቲዎቹ ጋር ተባብሮ በመስራቱ በርካታ ለውጥ አምጥቷል።

“የትምህርት ጥራትን በማሻሻል፣የጥናትና ምርምር አቅምን በፋይናንስ፤ በዓቅም ግንባታና በቴክሎጂ በመደገፍ አሁን ለደረሱበት ደረጃ እንዲበቁ የኖርዌይ መንግስት የላቀ ስራ ሰርቷል” ብለዋል።

መምህራንን በሁለተኛና ሶስተኛ ዲግሬ መርሃ-ግብር እንዲሰለጥኑ በማድረግ የዩኒቨርሲቲዎቹ የማስተማር አቅም እንዲሻሻል በዘመናዊ ላብራቶሪ፤በቤተ-መፃህፍት፤ በኮምፒውተር ቴክኖሎጂዎች እንዲደራጁ ማድረጉንም አስታውቀዋል።

ለሴቶችና አካል ጉዳተኛ ተማሪዎች በፋይናንስና በቴክኒክ በመደገፍና ምርምሮቻቸውን በማገዝ መልካም ስራ ማከናወኑንም ዶክተር ደስታ ተናግረዋል።

ድርቅን የሚቋቋሙ የገብስ ዝርያዎች እንዲስፋፉ የሚደረገውን ጥረት ከማገዝ ባለፈ በሃይል አጠቃቀም፣በፍራፍሬ ምርትና በሌሎችም የግብርና ስራዎች ዩኒቨርሲቲዎቹ ለሚያከናውኗቸው ስራዎች የኖርዌይ እገዛ ከፍ ያለ መሆኑን አስረድተዋል።

የሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ፍስሃ ጌታቸው በበኩላቸው፣ የሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ የዲፕሎማ ኮሌጅ እያለ ጀምሮ በአይሲቲ ቴክኖሎጂ፤በዘመናዊ የላብራቶሪ እቃዎችን በማደራጀት 280 የስርዓተ-ትምህርት ዝግጅቶችና ጥናቶችን በገንዘብ መደገፉን አስታውቀዋል።

“98 የሃዋሳ ዩኒቨርስቲ መምህራን በዶክተሬት ዲግሪ ደረጃ ተምረው ዩኒቨርሲቲውን እንዲያገለግሉ ያደረገው ድጋፍ ሁሌም የሚታወስ ነው” ያሉት ዶክተር ፍስሃ 36 የተለያዩ የተሻሻሉ የሰብል ዝሪያዎችን በማበልፀግ አርሶ አደሮች የተሻለ ምርት እንዲያገኙ ማድረጉንም ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ የኖርዌይ አምባሳደር ማሬት ለንዴሞ እንዳሉት፣በዩኒቨርሰቲዎቹ የሴት መምህራንን ተሳትፎ በማጠናክር መንግስታቸው ትኩረት በማድረግ ሰርቷል።

የኖርዌይ መንግስት ዩኒቨርሲቲዎቹ በጥናትና ምርምና የቴክኖሎጂ ሽግግርን እንዲያሳድጉ የጀመራቸውን ድጋፎች አሁንም አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

በጥናትና ምርምር፣በቴክኖሎጂ ፈጠራና በሌሎችም ያለውን ልምድ በማካፈል ለኢትዮጵያ ዘላቂ ልማት የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥል የተናገሩት ደግሞ በኖርዌይ የስነ-ህይወት ሳይንስ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ፈጠራ ምክትል ቻንስለር ፕሮፌሰር ጀሰቲን ጆንሰን ናቸው።

ዩኒቨርሲቲያቸው በቀጣይ ከሁለቱ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር የሚያደርገውን ትብብር በማሳደግ የተሻሉ ተሞክሮዎች እንዲስፋፉ እንደሚያደርግም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም