በከተማዋ በኢንዱስትሪና ግብርና ምርቶች ላይ ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ ታይቷል

55

አዲስ አበባ የካቲት 20/ 2011 በከተማዋ በኢንዱስትሪና ግብርና ምርቶች ላይ የተደረገው የዋጋ ጭማሪ እንዳስመረራቸው አንድ አንድ ሸማቾች ተናገሩ፡፡

የፌዴራል ንግድ ወድድርና ሸማቾች ጥበቃ ባለስልጣን  በምርቶች ላይ ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ ባደረጉ ድርጅቶች ላይ እርምጃ እወስዳለሁ ሲል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ በበኩሉ የአቅርቦት እጥረቱን ለመቅረፍ እስራለሁ ብሏል፡፡

በጥራጥሬ ምርቶች መጠነኛ ጭማሪ መታየቱን፣ በተለይም ምስር ላይ የአቅርቦት እጥረት መኖሩና በኪሎ 52 ብር ይሸጥ የነበረው  በ64 ብር እየተሸጠ መሆኑን  የነገሩን የከተማዋ ነዋሪ አቶ ሰዒድ ከማል ናቸው፡፡

አቶ ሰኢድ እንዳሉት ተልባና ሌሎች የቅባት እህሎችን በአቅርቦት እጥረት ምክንያት በገበያ ላይማግኘት እንዳልቻሉ ተናግረዋል፡፡

“በአዲስ አበባ ጥቃቅን ከምትላቸው ሸቀጦች እስከ ትልልቅ ምርቶች ዋጋ ያልጨመረ የለም ማለት ይቻላል” ያሉት ሌላው  ሸማች አቶ እንዳልካቸው አሰፋ የአንድ አንድ ምርቶች ዋጋ ጭማሪ ከፍተኛ መሆኑንም ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም በ12 ብር ይገዛ የነበረው ፓስቼራይዝድ ወተት 15 ብር መድረሱን እና የቢራ ዋጋ ጭማሪንም በማሳያነት አንስተዋል፡፡

መንግስት ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያለውን ማህበረሰብ ለመጥቀም ብሎ በሸማች ህብረት ስራ ማህበራት አማካኝት በተመጣጣኝ ዋጋ የሚያቀርባቸው ስኳር፣ ዘይትና ሌሎች ሸቀጦችን ሆቴሎች እና ሌሎች ነጋዴዎች ህጋዊ ባልሆነ መንገድ እየተጠቀሙበት ነው ሲሉም ነው አቶ እንዳልካቸው ትዝብታቸውን የተናገሩት፡፡

“መንግስት የገበያውን ስርዓት በደንብ ሊፈትሸው ይገባል” ያሉት አቶ እንዳልካቸው ህብረተሰቡን እያስመረረ  ያለው የኑሮ ውድነትም ሊፈታ ይገባል ብለዋል፡፡

በቂርቆስ ገበያ ማዕከል የተለያዩ ሸቀጣ ሸቀጦች ነጋዴ የሆኑት አቶ ወገኔ ፈረደ  በሸቀጦች ላይ የሚታየው የዋጋ ጭማሪ አስመጪዎች ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት ሸማቹን ህብረተሰብ ያላገናዘበ ጭማሪ በማድረጋቸው ነው ይላሉ፡፡

“ በተለይም ብቸኛ አስመጪ የሆኑት ነጋዴዎች ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ እያደረጉ ነው” ያሉት  አቶ ወገኔ፣ “እኛም ከአስመጪዎቹ በውድ ዋጋ የምናስመጣቸው ሸቀጦች ላይ የዋጋ ጭማሪ በምናደርግበት ወቅት ደንበኞቻችን ቅሬታ እያቀረቡብን ነው” ብለዋል፡፡

የህፃናት ወተት፣ ዳይፐርና ኤርያል የመሳሰሉ የፅዳት ሳሙናዎች ከቅርብ ግዜ ወዲህ ዋጋቸው መጨመሩንም አቶ ወገኔ ይናገራሉ፡፡

የንግድ ስርዓቱን በማስተካከል አማራጭ አስመጪዎች እንዲበራከቱም መስራት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

የአትክልት እና ፍራፍሬ ነጋዴ ወይዘሮ መሰረት አምዴ፤ ብርቱካን ላይ ባለው የአቅርቦት እጥረት ከፍተኛ የዋጋ ጭማሬ ማሳየቱንና ከዚህ ቀደም በ35 ብር ይገዛ የነበረው በአሁኑ ግዜ እስከ 70 ብር መድረሱን ተናግረዋል፡፡

በአገሪቱ በቂ የአትክልት እና ፍራፍሬ ምርት ቢኖርም በገበያ ሰንሰለቱ ደላሎች በመኖራቸው የዋጋ ንረት እንዲኖር እያደረጉ ነው በማለትም ገልጸዋል።

“በተለይም የግብርና ምርቶች ላይ አምራቹም ሆነ ሸማቹ የሚገባውን ዋጋ እያገኘ እና በተመጣጣኝ ዋጋ እየገዛ አይደለም” ያሉት ወ/ሮ መሰረት በመሃል የማይገባቸውን ጥቅም የሚያገኙ  ደላሎችን ስርዓት ማስያዝ ያስፈልጋል ብለዋል።

በንግድ ወድድር እና ሸማቾች ጥበቃ ባለስልጣን የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ አልቃዲር ኢብራሂም እንዳሉት ችግሩን ለመፍታት የዋጋ ጭማሪ የተደረገባቸው  ምርቶችን በመለየት ጥናት እየተካሄደባቸው መሆኑን  ተናግረዋል፡፡

ከእነዚህም በተጨማሪ  ታሽጎ የሚሸጡ የህፃናት ወተትና  ውሃ በስምምነት በሚመስል መልኩ ሁሉም ተመሳሳይ የዋጋ ጭማሪ በማድረጋቸው ስለተገቢነቱ ጥናት እየተካሄደ እንደሆነ የገለጹት አቶ አልቃዲር  ፍትሃዊ የገበያ ውድድር ባለበት ሁኔታ ሁሉም ዓይነት ምርቶች በተመሳሳይ ወቅት ተመሳሳይ ዋጋ ጭማሪ ማድረግ አይቻልም ብለዋል፡፡

“ቢራ ላይ በተደረገ የዋጋ ጭማሪ ሰፊ ጥናት ተካሂደዋል” ያሉት አቶ አላቃዲር ጥናቱ በመጠናቀቅ ላይ እያለም ሌላ ጭማሪ ተደርጓል ብለዋል፡፡

የጥናቱ ግኝት በቅርብ ግዜ ይፋ ይደረጋል ያሉት ሃላፊው አሳማኝ ኢኮኖሚያዊ ምክንያት የሌለው  የዋጋ ጭማሪ ባደረጉ ድርጅቶች ላይ እርምጃ  እንደሚወሰድም አብራርተዋል።

የንግድ ዘርፍ አለመዘመን እና በአስመጪነት በንግድ ዘርፍ የተሰማሩ ባለሃብቶች ቁጥር አናሳ መሆን ለዋጋ ንረቱ ዋነኞቹ ምክንያቶች መሆናቸውንም አቶ አልቃዲር ተናግረዋል፡፡

የአዲስ አበባ ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ ሃላፊ አማካሪ አቶ መከታ አዳፍሬ በምርቶች አቅርቦት እጥረት ምክንያት አልፎ አልፎ  የዋጋ መናር ተስተውሏል ነው ያሉት፡፡

በግብርናና ኢንዱስትሪ  ምርቶች የሚስተዋለውን የዋጋ ንረት ለመከለካል በሸማች ህብረት ስራ ማህበራት አማካኝነት ወደ ከተማ የማስገባት ሥራ እየተሰራ  መሆኑንም ተናግረዋል።  

አቶ መከታ እንዳሉት በከተመዋ የሚገኙ 141 መሰረታዊ ሸማች ህብረት ስራ ማህበራት እጥረት የተፈጠረባቸው የግብርና ምርቶች ከአጎራባች ክልሎች በማስገባት በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያቀርቡ እየተሰራ ነው፡፡

በከተማዋ የሚገኙ ሸማች ህብረት ስራ ማህበራት በመንግስት ድጎማ የሚቀርቡ መሰረታዊ ሸቀጦች በፍትሐዊነት ማከፋፈል እንዲቻል አዲስ አሰራር እየተዘረጋ ነው ብለዋል።   

በቂ ምርት እያለ የአቅርቦት ችግር እንዳለ በማስመሰል ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ ነጋዴዎች እንዳሉ የጠቆሙት ሃላፊው እነዚህ ነጋዴዎች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ስርዓት ለማስያዝ ይሰራል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም