ጃፓን ከ49 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የህክምና መሰረተ ልማት አውታሮች ግንባታና የህክምና ቁሳቁሶች ድጋፍ አደረገች

55

አዲስ አበባ የካቲት 19/2011 የጃፓን መንግስት ከ49 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የህክምና መሰረተ ልማት አውታሮች ግንባታና የህክምና ቁሳቁሶች አቅርቦት ድጋፍ አደረገ።

ለአማራ ክልላዊ መንግስት የተደረገው ይህ ድጋፍ የቀረበው በጃፓን ወርልድ ቪሽን በኩል ሲሆን የእናቶችንና አዲስ የሚወለዱ ህፃናትን ጤና ለማሻሻል ተግባር የሚውል መሆኑን በኢትዮጵያ የጃፓን ኤምባሲ ዛሬ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በላከው መግለጫ አመልክቷል።

ላለፉት ሶሰት ዓመታት ተግባራዊ የሆነው የድጋፍ ፕሮጀክቱ 14 የጤና ጣቢያዎችን ለማጠናከር የተካሄደ ነው።

ፕሮጀክቱ የመድሃኒትና ህክምና ቁሳቁስ አቅርቦትን ጨምሮ የድንገተኛና የሪፈራል ህክምና ስርዓት የማጠናከር፣ የሰራተኞችንና የኮሙዩኔኬሽን ባለሙያዎችን አቅም የመገንባትና ሌሎች ተያያዥ ተግባራትን ያካትታል።  

የህክምና መሰረተ ልማቱና ቁሳቁስ ርክክብ በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ዳሱኪ ማቱሱንጋ፣ የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር አበባው ገበየውና የጃፓን ወርልድ ቪሽን ብሄራዊ ዳይሬክተር ሚስተር ኤድዋርድ ብራውን በተገኙበት ተካሂዷል።

ጃፓን አገሯ በሚገኙ የተለያዩ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች አማካኝነት ኢትዮጵያ ውስጥ በትምህርትና በጤና የልማት መስኮች ድጋፍ እያደረገች ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም