በከባድ የሙስና ወንጀል የተከሰሱት የአቶ ኢሳያስ ዳኘው የክስ መቃወሚያ ቀረበ

298

አዲስ አበባ የካቲት 19/2011 በከባድ የሙስና ወንጀል የተከሰሱት የአቶ ኢሳያስ ዳኘው የክስ መቃወሚያ ቀረበ።

የካቲት 13 ቀን 2011 ዓ.ም ኢሳያስ ዳኛው ከ44 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር የአሜሪካ ዶላር በላይ በሚሆን ከባድ የሙስና ወንጀል ተጠርጥረው አቃቤ ህግ ክስ እንደተመሰረተባቸው ይታወሳል።

ተከሣሽ በኢትዮ ቴሌኮም የኤን.ጂ.ፒ.ኦ. (N.G.P.O.) ዳይሬክተር ሆነው ሲሰሩ የተጣለባቸውን ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊነት ወደጎን በመተው በተሰጣቸው የሥራ ሥልጣን መሠረት ዜድ.ቲ.ኢ. (ZTE) ከተባለ የቻይና ኩባንያ ጋር ከ44 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር በላይ የግዥ ውል ለጊዜው ስማቸው በክሱ ውስጥ ካልተጠቀሱ (እና ካልተያዙ) ግብረአበራቸው ጋር ቀጥታ ግዥ እንዲፈጸም በማድረግ ተከሰዋል።

በዚህም በስውር ጥቅም በመመሳጠር በመንግሥትና በኮርፖሬሽኑ የተሰጣቸውን ሹመት፣ ሥልጣን ወይም ኃላፊነት በግልጽ ተግባር ወይም በግድፈት ያላግባብ ተገልግለዋል ሲልም የአቃቤ ህግ ክስ ያመለክታል።

እንዲሁም ተከሳሹ ከሥልጣን በላይ አልፎ በመስራት የማይገባውን ጥቅም ለዜድ.ቲ.ኢ. (ZTE) ለማስገኘት እና በመንግሥትና በኢትዮ ቴሌኮም ኮርፖሬሽን ጥቅም ላይ ጉዳት እንዲደርስ አድርገዋል ይላል የአቃቤ ህግ ክስ።

ተከሣሽ ለዩኒቨርሲቲዎች የኔትዎርክ ግንባታ የአገልግሎት ግዥ ውል ኤን.ጂ.ፒ.ኦ. ሊጠቀምበት ይገባ የነበረውን የግዥ ማንዋል ያልተጠቀሙና በኢትዮ ቴሌኮም የግዥ መመሪያ፣ ፖሊሲና የሥነ-ሥርዓት ማንዋል እና በሌሎች አግባብነት ባላቸው የግዥ ሕጎች መሠረት በግልጽ ጨረታ በማወዳደር ከፍተኛ ብቃት ያላቸውን ተወዳዳሪዎች በመጋበዝ ከጊዜ፣ ከሀብትና ከቴክኖሎጂ አኳያ የተሻለውን መግዛት ሲገባው የግዥ ሥራን በማያመች አኳኃን በመምራትና በማስፈፀም በኢትዮ ቴሌኮም ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንዲደርስ ያደረጉ በመሆናቸው በመላ ሃሳባቸውና በወንጀል ድርጊቱና በውጤቱ በሙሉ ተካፋይ በመሆን በዋና ወንጀል አድራጊነት የመንግሥትን ሥራ በማያመች አኳኋን በመምራት ከባድ የሙስና ወንጀል አቃቤ ህግ መክሰሱ ይታወሳል።

የካቲት 13 ቀን 2011 ዓ.ም የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 15ኛ ወንጀል ችሎት ቀርበው ክሳቸው ተነቦ እንዲረዱት የተደረገ ሲሆን የክስ መቃወሚያቸውን ይዘው ለመቅረብ ፍርድ ቤቱ ለዛሬ ተለዋጭ ቀጠሮ መስጠቱ አይዘነጋም።

በዚሁ መሰረት አቶ ኢሳያስ ዳኘው በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 15ኛ ወንጀል ችሎት ቀርበው በጠበቃቸው በኩል የክስ መቃወሚያቸውን አቅርበዋል።

የተከሳሽ ጠበቃ አቃቤ ህግ በክሱ ውስጥ ካልተጠቀሱት (እና ካልተያዙ) ግብረ አበራቸው ጋር በመሆን የሚለው ግብረ አበሮቹ እነማን እንደሆኑ የማይገለጽ እንደሆነና ተከሳሽ ከነማን ጋር አብረው ወንጀሉን ፈጸሙ የሚለው ጉዳይ በዝርዝር መቀመጥ እንዳለበት ገልጸዋል።

በክሱ ቻርጅ ላይም ግብረ አበሮች ዝርዝር አለመካተቱ ወንጀሉን ፈጸሙ የተባሉ ሰዎች በግልጽ በወንጀል ውስጥ ያላቸውን ተሳትፎ ለማወቅ እንደሚያዳግት ተናግረዋል።

የምስክር ቃል ወደ መስማት በሚገባበት ጊዜ ወንጀሉን ፈጸሙ የተባሉት ግብረ አበሮች ዝርዝር መታወቅ ስላለበት አቃቤ ህግ ግብረ አበሮች ተብለው ስማቸው ያልተገለጹ ግለሰቦችን በክስ ቻርጅ ውስጥ ዘርዝሮ ማስቀመጥ አለበት ብለዋል።

በክሱ ላይ በዋና ወንጀል አድራጊነት የሚለውም ጉዳይ ግብረ አበር የተባሉት ሰዎች ግለሰቦች ሳይታወቁና በወንጀል ውስጥ ያላቸው ተሳትፎ በግልጽ ባልተቀመጠበት ሁኔታ የወንጀሉ ዋና ፈጻሚ ተብለው መቀመጣቸውም የግልጽነት ጥያቄ እንደሚያስነሳም አመልክተዋል።

ዜድ.ቲ.ኢ. (ZTE) የተባለው የቻይና ኩባንያ ባለቤትነቱ መንግስት ሆኖ ሳለ በክሱ ላይ ተካሳሽ ከዜድ.ቲ.ኢ. ስራ አስኪያጅ ጋር በስውር በመመሳጠር የሚለው ነገር ተካሳሽ ከቻይና መንግስት ጋር በስውር የተመሳጠሩት የሚል አንድምታ እንዳለው ጠቅሰዋል።

ስለዚህም ተካሳሽ የተመሳጠሩት ከቻይና መንግስት ጋር ነው የሚል ነገር ስላለ አቃቤ ህግ በዜድቲኢ ውልና ግዢ ጉዳይ ላይ ያለውን ነገር በዝርዝር ማስቀመጥ አለበት ብለዋል።

በተጨማሪም በክሱ ላይ ተከሳሽ ኢትዮ ቴሌኮም ከዜድ.ቲ.ኢ. ስራ የተደረገውን የግዥ ውል በማሻሻል አለአግባብ ተጠቅመዋል የሚል ነገር እንዳለና ይህም የሚያሳየው ከዚህ በፊት በተቋማቱ መካከል የነበረ ውል እንዳለ የሚያመላክት በመሆኑ ከመሻሻሉ በፊት ነበረ ስለተባለው ውል አቃቤ ህግ በግልጽ ማስቀመጥ አለበት ሲሉም ተቃውመዋል።

በክሱ ቻርጅ ላይ ‘በኢትዮ ቴሌኮም የኤን.ጂ.ፒ.ኦ. (N.G.P.O.) ዳይሬክተር በነበሩበት፣ ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊነት ወደ ጎን በመተውና የተሰጣቸውን ከፍተኛ ስልጣን በአግባቡ በመጠቀም’ እንደሚልና ይህም የተካሳሽ የስልጣን ደረጃ በግልጽ የማያሳይ ነው በማለት ጠበቃው ገልፀዋል።

በሙስና ወንጀል ውስጥ ሃላፊነት፣ ስልጣንና ሙያ የሚባሉት ጉዳዮች የተለያየ ትርጓሜ እንዳላቸውና የስልጣን ደረጃቸው በግልጽ አለመቀመጡ በየትኛው የስልጣን ደረጃ ተከሳሽ ይሄን ፈጸሙ የሚለውን ጉዳይ በግልጽ እንደማያመላክት ነው ጠበቃው ለችሎቱ ያስረዱት።

በተያያዘም የተጣለባቸውን ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊነት እንዲሁም የተሰጣቸውን ሹመት፣ ሥልጣን ወይም ኃላፊነት የሚለው ጉዳይ ተከሳሽ የስልጣን ምንጫቸው ማን እንደሆነ ስልጣናቸውን በምን አግባብ ነው ያገኙት ከሚለው ጉዳይ ጋር ተያይዞ ግልጽነት የለውም ብለዋል።

በሌላ በኩል ከተሰጣቸው ሥልጣን በላይ አልፎ በመስራት የማይገባቸውን ጥቅም ማግኘት በሌላ በኩል ስልጣናቸውን አለአግባብ መጠቀም የሚል ነገር እንዳለና ይሄም ስልጣናቸው ምንድነው የሚለው ነገር እርስ በእርሱ የሚጣረስ ሀሳብ እንደሆነም ተናግረዋል።

በወንጀል ውስጥ ከፍተኛ ጉዳት የሚባል ጉዳይ እንደሌለና አቃቤ ህግ ጉዳዩ የኢኮኖሚ ወንጀል በመሆኑ ተካሳሽ ያደረሰውን ጉዳት በመጠን ማስቀመጥ እንዳለበት፡ ካልሆነም በገንዘብ የማይተመን ጉዳት አድርሷል በሚል ማቅረብ እንደሚገባውም አመልክተዋል።

ክስ ውስጥ ወንጀሉ የተፈጸመበትን ጊዜ በክስ ቻርጅ ውስጥ እንዳላስቀመጠ ገልጸው ይህም አለመሆኑ በአጠቃላይ ተፈጸሙ የተባሉት ድርጊቶች መቼ እንደተፈጸሙ ለማወቅ እንደማይቻል ገልጸዋል።

ዋናው ክስ ከዜድ ቲ ኢ ጋር የተያያዘ ሆኖ ሳለ  ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በተያያዘ ለዩኒቨርሲቲዎች የኔትዎርክ ግንባታ የአገልግሎት ግዥ ውል ጋር የተያዘው ክስ ለምን ቦክስ ቻርጅ ውስጥ እንደተካተተ ግልጽ አይደለም ሲሉም ጠይቀዋል።

ከዩኒቨርሲቲዎች የኔትዎርክ ግንባታ አገልግሎት ግዥ ጋር በተያያዘ በሌሎች አግባብነት ባላቸው የግዥ ሕጎች መሠረት በግልጽ ጨረታ በማወዳደር ከፍተኛ ብቃት ያላቸውን ተወዳዳሪዎች በመጋበዝ ከጊዜ፣ ከሀብትና ከቴክኖሎጂ አኳያ የተሻለውን መግዛት ሲገባው በሚለው ጉዳይ ላይ ሌሎች አግባብነት ያላቸው ህጎች የሚለው በግልጽ መቀመጥ እንዳለበት ገልጸዋል።

በተጨማሪም ኢትዮ ቴሌኮም የግዥ መመሪያ፣ ፖሊሲና የሥነ-ሥርዓት ማንዋል የሚለውም በመመሪያ ፖሊሲና የስነ ሰርአት ማንዋል ውስጥ ተካሳሹ ጣሱት የተባለው ነገር ማብራሪያ የሚፈልግ መሆኑንም አመልክተዋል።

በክሱ ላይ ከተሰጣቸው ሥልጣን በላይ አልፎ በመስራት የማይገባውን ጥቅም ለማገኘት እንዲሁም ለዜድ.ቲ.ኢ. (ZTE) ለማስገኘት እና በመንግሥትና በኢትዮ ቴሌኮም ኮርፖሬሽን ጥቅም ላይ ጉዳት እንዲደርስ የሚለው ጉዳይ ተካሳሽ የትኛውን ጥቅም ነው ያሳጡት፤ መንግስትና ኢትዮ ቴሌኮም ያጡት ጥቅም በግልጽ መቀመጥ አለበት ብለዋል።

በተጨማሪም ለራሳቸው ጥቅም ወይም ሌሎችን ለመጥቀም በሚል በክስ ውስጥ የተቀመጡ ጉዳዮች ፍርድ ቤቱ ምርጫ ውስጥ እንዲገባ በሚያደርግ መልኩ መቀመጥ እንደሌለበትና የራሳቸውና የሌሎች የሚለው ተይቶ መቀመጥ አለበት ሲሉም ተቃውመዋል።

ክሱ በአጠቃላይ የሀሳብ መደራረብና ድገግሞሽ ያለበት፤ ግልጽነት የጎደለው በመሆኑ ክሱ ተካሳሹ በግልጽ ሊረዳው በሚችልበት ሁኔታ በዝርዝር መቅረብ እንደላበት ጠበቃው ለችሎቱ በቃል የክስ መቃወሚያቸውን አቅርበዋል።

ፍርድ ቤቱ አቃቤ ህግ በቀረበው የክስ መቃወሚያ ላይ ምላሽ እንዲሰጥ ቢጠይቅም የክሱ ጉዳይ ‘የያዝነው በቡድን በመሆኑ’ ምላሽ ለመስጠት አጭር ጊዜ ተለዋጭ ቀጠሮ እንዲሰጠው ጠይቋል።

የተከሳሽ ጠበቃ በበኩላቸው በወንጀል ህጉ መሰረት የተከሳሽ ጠበቃ የቃል መቃወሚያ ሲያቅርብ አቃቤ ህግ ለመቃወሚያው ወዲያው ምላሽ መስጠት አለበት ስለዚህም ምላሽ ይስጥ ሲሉ ተከራክረዋል።

ፍርድ ቤቱም የቀረበው የክስ መቃወሚያ ስፋት ያለው በመሆኑ ጊዜ የሚጠይቅ መሆኑን እንደሚያምን በመግለጽ አቃቤ ህግ በክስ መቃወሚያ ምላሽ ይዞ እንዲቀርብ ለየካቲት 22 ቀን 2011 ዓ.ም ከረፋዱ 4 ሰአት ከ30 ደቂቃ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።