የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተደራሽ ባለመሆኑ ለመስኖ የተቆፈሩ ጉድጓዶች ጥቅም ላይ አልዋሉም--- አርሶ አደሮች

81

ማይጨው የካቲት 18/2011 የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተደራሽ አለመሆን ለመስኖ ልማት የተቆፈሩ ጥልቅ የውሃ ጉድጓዶች ለሰባት ዓመት ያለጥቅም እንዲቀመጡ ማድረጉን በትግራይ ክልል የራያ ዓዘቦ ወረዳ አርሶ አደሮች ገለፁ።

የራያ አላማጣ ወረዳ አርሶ አደሮችም በኤሌክትሪክ አገልግሎት መቋረጥ የመስኖ ሥራቸውን በአግባቡ ለማከናወን እንዳልቻሉ ተናግረዋል።

የክልሉ ውሀ ሀብት ቢሮ በወረዳዎቹ በመስኖ ልማት ዘርፍ እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን ለይቶ መፍታት ላይ ዓላማው ያደረገ የውይይት መድረክ በአላማጣ ከተማ አካሂዷል።

በራያ ዓዘቦ ወረዳ የማሩ ቀበሌ አስተዳዳሪ አርሶ አደር ተመስገን ከበደ በወቅቱ እንዳሉት አርሶ አደሩን በመስኖ ተጠቃሚ ለማድረግ በማሰብ ከሰባት ዓመት በፊት ስድስት ጥልቅ የውሃ ጉድጓዶች ተቆፍረዋል።

ይሁንና በኤሌክትሪክ አገልግሎት መቆራረጥና መስመር አለመዘርጋት ምክንያት የተቆፈሩ ጥልቅ የውሃ ጉድጓዶች ለዓመታት ለመስኖ ልማት አገልግሎት ሳይውሉ መቆየታቸውን ገልጸዋል።

ከውሃ ጉድጋዶቹ መካከል አራቱ የኤሌክትሪክ መስመር ስላልተዘረጋላቸው ያለአገልግሎት መቀመጣቸውን ተናግረዋል።

"የኤሌክትሪክ መስመር የተዘረጋላቸው ሁለት የውሃ ጉድጓዶችም በየጊዜው በሚያጋጥም የኃይል መቆራረጥ ተገቢውን አገልግሎት እየሰጡ አይደሉም" ብለዋል።

በወረዳው ዋርግባ ቀበሌ ለመስኖ ልማት ከተቆፈሩ አምስት ጥልቅ የውሃ ጉድጓዶች ውስጥ ጥቅም ላይ የዋሉት ሁለት ብቻ መሆናቸውን የገለፁት ደግሞ አርሶ አደር ዝናቡ ሀዲስ ናቸው፡፡

"ለሦስቱ የውሃ ጉድጓዶች የተገጠመላቸው ትራንስፎርመሮች በመቃጠላቸው አገልግሎት እየሰጡ አይደለም " ብለዋል ።

"በተቆፈሩልን የውሃ ጉድጓዶች ተጠቀመን የመስኖ ልማት እያካሄድን ቢሆንም በተጋነነ የፍጆታ ክፍያ ሳቢያ የኤሌክትሪክ አገልግሎት እንዲቋረጥብን መደረጉ አግባብ አይደለም" ያሉት ደግሞ በራያ አላማጣ ወረዳ የልማዓት ቀበሌ ነዋሪ አርሶአደር አያሌው ንጉሰ ናቸው፡፡

በመስኖ አምርተው የሚያገኙት ገቢና ለኤሌክትሪክ ፍጆታ የሚጠየቁት ከፍተኛ ክፍያ የተመጣጠነ ባለመሆኑ በምርት ሂደት ላይ የሚጠየቁትን የአገልግሎት ክፍያ መፈፀም እየተሳናቸው መሆኑን ተናግረዋል ።

"ለምንጠቀምበት የኤሌክትሪክ ኃይል ፍጆታ ክፍያ ልንጠየቅ የሚገባው ያመረትነውን ምርት ከሸጥን በኋላ ነው" ያሉት ደግሞ ሌላው የቀበሌው ነዋሪ  አርሶ አደር አያሌው ንጉሴ ናቸው፡፡

"በክፍያ ምክንያት አገልግሎቱ እንዲቋረጥ መደረጉ ልማቱን እያሰተጓጎለብን በመሆኑ ፈጣን መፍትሄ ሊሰጠን ይገባል" ሲሉ ቅሬታቸውን ገልፀዋል ።

በክልሉ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የአላማጣ ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ አቶ ቢያድግልኝ ሞላ በወረዳዎቹ ለውሃ ጉድጓዶች ተገጥመው የነበሩ የኤሌክትሪክ ትራንስፎርመሮች የጥራት ደረጃቸውን የጠበቁ ባለመሆናቸው የኃይል መቋረጥ ማጋጠሙን ተናግረዋል ።

ከፍተኛ የኃይል ፍሰትና የመብረቅ አደጋ መከላከያ ያልነበራቸው መሆናቸውም ለችግሩ ተጨማሪ ምክንያት መሆኑን ነው ያስረዱት ።

የኤሌክትሪክ ቆጣሪዎች በየጊዜው ስለሚበላሹም አርሶ አደሩ ለሚጠቀምበት ፍጆታ በግምት ተተምኖ እንዲከፍል መደረጉ ለተጋነነ ወጭ ሲዳርገው መስተዋሉንም አስረድተዋል።

በአሁኑ ወቅት በመስሪያ ቤቱ በተፈጠረው አዲስ አደረጃጀት መሰረት በፌዴራል ይከናወን የነበረው በቅርንጫፍ እንዲከናወኑ የተወሰነ በመሆኑ ቀደም ሲል የነበሩት ችግሮች እንደሚፈቱ ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም አሁን ባለው አዲስ አደረጃጀት የንብረት ግዢ በክልል ደረጃ እንዲፈፀም የተፈቀደ መሆኑና የውጭ ምንዛሬ እጥረት እየተቃለለ በመምጣቱ የነበሩ ችግሮች እንደሚፈቱ አመልክተዋል።

በክልሉ ውሃ ሀብት ቢሮ የመስኖ ልማት ዳይሬክቶሬት ተወካይ አቶ ተስፋአለም ገብረ በበኩላቸው በወረዳዎቹ  የተቆፈሩ የውሃ ጉድጓዶችን ወደ ስራ ለማስገባት ከክልሉ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ጽህፈት ቤት ጋር  በጋራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል ።

በወረዳዎቹ ለተበላሹ 90 ጥልቅ የውሃ ጉድጓዶች የትራንስፎርመር ጥገና፣ የውሃ መሳቢያ ፓምፖች ቅየራ ሥራና ሌሎች ተጓዳኝ ስራዎችም እየተከናወኑ መሆናቸውን አስታውቀዋል ።

እንደ ተወካዩ ገለጻ በግማሽ ዓመቱ 27 ጥልቅ የውሃ ጉድጓዶች ጥገና ተደርጎላቸው ዳግም አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ ተችሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም