የሶስት የስፖርት አይነቶች አሰልጣኞች ስልጠና ተጀመረ

185
አዲስ አበባ ግንቦት 21/2010 የእግር ኳስ፣ አትሌቲክስና የቮሊቦል አስልጣኞች የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ የአሰልጣኝነት ስልጠና ዛሬ በኢትዮጵያ ወጣቶችና ስፖርት አካዳሚ  ተጀምሯል። ስልጠናውን የኢትዮጵያ ወጣቶችና ስፖርት አካዳሚ እንዲሁም የእግር ኳስ፣ አትሌቲክስና ቮሊቦል ፌዴሬሽኖች በጋራ አዘጋጅተውታል። 200 ሰልጣኞች የሚሳተፉ ሲሆን የአትሌቲክስና የእግር ኳስ አሰልጣኞች የሁለተኛ፤ የቮሊቦል የአንደኛ ደረጃ የአሰልጣኝነት ስልጠና እንደሚወስዱ ተገልጿል። የወጣቶችና ስፖርት አካዳሚ ከፍተኛ የአቅም ግንባታ ባለሙያ ወይዘሮ እመቤት ታከለ ለኢዜአ እንደገለጹት ስልጠናው በስፖርቶቹ ብቁና አቅማቸው የተገነባ የስፖርት ባለሙያዎችን ለማፍራት የበኩሉን አስተዋጽኦ ያደርጋል። አካዳሚው ከያዛቸው ግቦች አንዱ በረጅም፣ በመካከለኛና በአጭር ጊዜ በሚሰጡ ስልጠናዎች ብቃት ያላቸው የስፖርት ባለሙያዎች ማፍራት እንደሆነና ዛሬም የተጀመረው ስልጠና የዚሁ ግብ አካል መሆኑን ገልጸዋል። በተለይም ከትምህርት ቤት ለተወጣጡ፣ የፕሮጀክት ወጣቶችን በማሰልጠን ላይ ላሉ እና በዘርፉ ለሚሳተፉ አካላት የአንደኛ ደረጃ የአሰልጣኞች ስልጠና መስጠት በራስ መተማመን እንዲኖራቸውና ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ የሚያግዝ፤ በአገር ደረጃ ተተኪ ለማፍራትም የሚረዳ ነው ብለዋል። ለአሰልጣኞች የንድፈ-ሀሳብና የተግባር ስልጠና የሚሰጣቸው ሲሆን በስልጠናው ማጠናቀቂያ ወቅት ደረጃቸውን ማሻሻል የሚችሉበት ፈተና እንደሚሰጣቸው ጠቁመዋል። አሰልጣኞች ከስልጠናው ያገኙትን ተሞክሮና ልምድ በተግባር በመቀየር በስፖርቶቹ ብቁ ተወዳዳሪዎችን ለማፍራት መስራት እንደሚገባቸው ነው ወይዘሮ እመቤት ያሳሰቡት። የአሰልጣኞች የደረጃ ስልጠናው እስከ ሰኔ 10 ቀን 2010  የሚቆይ ይሆናል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም