የማምረቻ ማሽኖችንና መለዋወጫ ቁሳቁሶችን በሀገር ውስጥ በማምረት ተጠቃሚ ሆነናል - ኢንተርፕራይዞች

79

አዲስ አበባ የካቲት 18/2011 ከውጭ በውድ ዋጋ የሚገቡ የማምረቻ ማሽኖችንና የማሽን መለዋወጫ ቁሳቁሶችን በሀገር ውስጥ በማምረት ተጠቃሚ መሆናቸውን ሁለት የኢንተርፕራይዝ ባለቤቶች ተናግረዋል።

በአዲስ አበባ ጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 የ3ኤ ብረታብረት ኢንተርፕራይዝ ህብረት ሥራ ማህበር ስራ አስኪያጅ አቶ አንዱአለም ሃይሉ እንዳሉት በ2004 ዓ.ም ከተቀጣሪ ሰራተኝነት ወደ ራሳቸው ሥራ ሲሸጋገሩ አነስተኛ ብር በማዋጣት ለ6 በመደራጀት ከግለሰብ ቤት በመከራየት ነው ስራ የጀመሩት፡፡

ስራውን ከጀመሩ በኋላ ተጠናክረው እንዲወጡ በመንግስት የመስሪያ ሼድ  ከመስጠት ጀምሮ  የብድርና የተለያዩ ድጋፎች እየተደረገላቸው እንደሆነም ይገልጻሉ።

”አጀማመራችን በጣም ትንሽ ቢሆንም እንኳ በነበረን የስራ ተነሳሽነትና የተደረገልን ድጋፍ አግዞን ከ40ሺህ ብር መነሻ ካፒታል በአሁኑ ሰዓት ወደ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ማንቀሳቀስ የሚያስችል የካፒታል አቅም ባለቤትነት ተሸጋግረናል” ነው ያሉት፡፡

ከውጭ በውድ ዋጋ የሚገቡ ማሽኖችን የሚተኩ የእንጨት መሰንጠቂያና መቁረጫ ማሽኖችን በመስራት በአዲስ አበባ እና በክልል ከተሞች ለተጠቃሚዎች በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ ላይ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡  

በኢንተርፕራይዙ የሚሰሩ ማሽኖች ከ10-15 የሰው ሃይል የሚያፈልግ የጣውላ ማምረት ተግባርን በ1 ወይም በ2 ሰው ብቻ እንዲሰራ የሚያስችል መሆኑና ለስራው ጥራትም ከፍተኛ ጥቅም እንዳለው ነው ያስረዱት፡፡

ማሽኑ በርካታ ምርቶችን በአጭር ጊዜ ለማምረት የሚያስችል አቅምና የተሻለ ጥራት ያለው በመሆኑ የገበያ ችግር እንዳልገጠማቸውም  ነው አቶ አንዱአለም የተናገሩት።

በኢንተርፕራይዙ ውስጥ ከ20 በላይ ቋሚና ጊዚያዊ ሰራተኞች እንዳሉዋቸው የነገሩን አቶ አንዱአለም መንግስት የማምረቻ ቦታ እንዲያገኙ መደረጉ ለውጤታማነታቸው ከፍተኛ አስተዋጽኦ እዳለውም ጠቅሰው፤በተመሳሳይ ጊዜ ብዙ መሽኖችን ለማምረት ግን የመስሪያ ቦታ ጥበት አጋጥሟቸዋል።

በኢንተርፕራይዙ የስራ እድል ተጠቃሚ የሆነው ወጣት ወገኔ ሃይሉ በሰጠው አስተያየት በኢንተርፕራይዙ ለ4 ዓመታት በስራ ላይ መቆየቱንና በቀን ስራ ሲያገኘው ከነበረው ዝቅተኛ ገቢ በአሁኑ ወቅት የተሻለ ክፍያ በማግኘቱ ከራሱ አልፎ ቤተሰብ እያገዘ ጎን ለጎንም እየቆጠበ መሆኑን ተናግሯል፡፡

ካሁን በፊት በቤተሰብ ድጋፍ ይኖር እንደነበር የሚገልጸው በኢንተርፕራይዙ ተቀጥሮ የሚሰራ ሌላው ወጣት መልኬ ባዬ፤ አሁን በወር 4ሺህ ብር ተከፋይ በመሆን ከራሴ አልፌ ቤተሰቦቼን መርዳት ጀምሬአለሁ ብሏል፡፡

በልደታ ክፍለከተማ ወረዳ 4 የሚገኝ የካሳዬ እና በለጠ ብረታብረት የሽርክና ስራ ማህበር ስራ አስኪያጅ አቶ በለጠ ብርሃኑ በበኩሉ  ከዛሬ 4 ዓመት በፊት ከጓደኞቻቸው ጋር በመሆን ከኪሳቸው በማዋጣትና የተወሰነ ብድር ከግለሰብ በመውሰድ በ17ሺህ ብር አነስተኛ ቤት ተከራይተው ስራ እንደጀመሩ ይናገራሉ፡፡

በተከራዩት ቤት የተወሰነ ጊዜ ከሰሩ በኋላ ግን በመንግስት በኩል የተሻለ ስፋት ያለው የመስሪያ ቦታ ተሰጥቷቸው ከ7 የማህበሩ አባላት በተጨማሪ ሌሎች ሰራተኞችን ጨምረው የተሻለ ስራዎችን በመስራት ላይ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

አሁን የነበረባቸውን ብድር ሙሉ ለሙሉ  በመክፈል ከ750 ሺህ ብር በላይ ካፒታል ባለቤት ለመሆን መቻላቸውንም አስረድተዋል፡፡

አቶ በለጠ እንደሚሉት የማህበሩ ዓላማ በውድ ዋጋ ከውጭ የሚገቡትን የመኪና እና የፕላስቲክ ውጤቶች ማምረቻ  ማሽነሪዎች መለዋወጫ እቃዎችን ለመተካት በትጋት መስራት ላይ ነው፡፡

በድርጅቱ ውስጥ ተቀጥረው የሚሰሩ ሰራተኞች ከቴክኒክና ሙያ ተቋማት የተመረቁ መሆናቸውንም አስረድተዋል፡፡

"ካሁን በፊት አምርተን ለገበያ ካቀረብናቸው ምርቶች መካከል የመኪና ሞተር ጥርሳጥርሶች፣ ሻፍቶችን፣ ዳሃዮችን እና አብዛኞቹ የፕላስቲክ ፋብሪካዎች መለዋወጫዎች ጥቂቶቹ ናቸው” ብለዋል፡፡

በኢንተርፕራይዙ በማሽን ሰራተኝነት ተቀጥሮ ሲሰራ  ያገኘነው ወጣት አባስ ደጉ እንዳለው ከቴክኒክና ሙያ ተመርቆ ለጊዜው ተቀጥሮ እየሰራ  ቢሆንም ለወደፊት ግን ከነሱ ተሞክሮ በመነሳት የስራ ልምዱን አዳብሮ የራሱን የመክፈት እቅድ እንዳለው ተናግሯል።

“የመስራት ፍላጎት ካለ ስራ አይጠፋም፤  በትምህርት ሲደገፍ ደግሞ የተሻለ ውጤታማ ያደርጋል” በማለትም ነው  ወጣት አባስ የገለጸው።

በኢንተርፕራይዙ አዲስ ሰራተኛ እንደሆነ የነገረን አቶ የማነ ዘሚካኤል”የስራ ተነሳሽነታቸው ስራ ለመስራት ጊዜ አለመምረጣቸው አስደሳች ነው፤ ለእድገት የሚታገሉ እንጂ ቀን እየቆጠሩ የሚሰሩ አይደሉም” ብሏል፡፡  

ኢንተርፕራይዞቹ መንግስት ያደረገላቸው ድጋፍ ለውጤት እንዳበቃቸውና በቀጣይም ወደ ከፍተኛ ኢንዱስትሪ ደረጃ ለማሳደግ እየሰሩ መሆኑን ነው የጠቀሱት፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም