የናይጀሪያ ምርጫ በሰላማዊ ሁኔታ መካሄዱ ተነገረ

59

የካቲት 18/2011 የናይጀሪያ ምርጫ በሰላማዊ ሁኔታ መካሄዱን የአፍሪካ ህብረት ታዛቢዎች ቡድን ገለጸ።

በቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ የሚመራው የአፍሪካ ህብረት ታዛቢዎች ቡድን ባለፈው ቅዳሜ የተካሄደው የናይጄሪያ ምርጫ ሰላማዊ እንደነበር ዛሬ ለህዝብ ይፋ አድርገዋል።

በምርጫው በዋና ተፎካካሪነት የቀረቡት ፕሬዚዳንት ሙሃሙዱ ቡሃሪ እና ተቀናቃኛቸው የቀድሞ ምክትል ፕሬዚዳንት አቲኩ አቡበከር የተሳተፉ ሲሆን ከፍተኛ ግምት ተሰጥቶትም ነበር።

በቁሳቁስ በሁሉም ቦታዎች አለመዳረስ ምክንያት ለአንድ ሳምንት ተራዝሞ የተካሄደው ምርጫ በሰላማዊ ሁኔታ መጠናቀቁን የአፍሪካ ህብረት የታዛቢዎች ቡድን ገልጿል።

የተወሰኑ የምርጫ ውጤቶች ዛሬ ሊገለጹ እንደሚችሉ ቢነገርም የምርጫው አሸናፊ መቼ ይፋ እንደሚደረግ አልታወቀም።

ተዓማኒና በአንጻራዊነት በተረጋጋ ሁኔታ እንደተካሄደ የተነገረለት የናይጀሪያ ምርጫ በሀገሪቱ የፖለቲካ ታሪክ አዲስ ምዕራፍ ሊከፍት ይችላል በሚል ውጤቱ እየተጠበቀ ነው።

“የናይጄሪያ የ2019 ምርጫ በአጠቃላይ በሰላማዊ ሁኔታ ነው የተካሄደው” ሲሉ የምርጫ ታዛቢዎች ቡድኑ መሪ አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ ገልጸዋል።

በአንጻሩ ከ70 በላይ የሲቪል ማህበራትን ያቀፈው ቡድን ትናንት እንደገለጸው ከምርጫው ጋር በተገናኘ 39 ሰዎች ተገድለዋል።

ምንጭ፦ሮይተርስ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም